ረቡዕ
የካቲት 13 ቀን 2005 ዓ.ም ከቀኑ 9፡00 ሰዓት አካባቢ ለአንድ ቀጠሮ ሜክሲኮ ተገኝቻለሁ፡፡ ከታክሲ እንደወረድኩም የቀጠርኩትን
ሰው ስደውልለት ገና መርካቶ እንደሆነ ነገረኝ፡፡ ፀሐዩዋ በጣም ታቃጥላለች፡፡ የአዲስ አበባ ሙቀት ከወትሮዉ በጣም የተለዬ ሆኖዋል፡፡
ጓደኛዬ እስከሚርስ ቦንዙር ከሚባል ካፌ ገብቼ አረፍ ለማለት አሠብኩ፡፡ ወደ ካፌው እያመራሁ እያለ በዕለቱ ከሚታተሙ ጋዜጦቸ መካከል
‘ሰንደቅ’ ጋዜጣ በፊት ገፁ አንድ በጣም አስገረሚ ርዕስ ይዞ ወጥቷል፡፡ “አቡነ ሳሙኤል ቀጣዩ ፓትርያርክ ለመሆን የምረጡኝ ዘመቻ ጀመሩ” የሚል፡፡ ጋዜጣውን ገዝቼ ወደ ካፌው ገባሁና
አረፍ ብዬ ጋዜጣዉን ማንበብ ጀመርኩ፡፡ ጋዜጣው ላይ እንዳነበብኩት ከሆነም አቡነ ሳሙኤል የምርጫ ቅስቀሳውን በተጠናከረ ሁኔታ እያካሔዱት
ነው ማለት ይቻላል፡፡ እንዴት እንደዚህ ሊሆን ይችላል? እግዚኦ እንጅ ሌላ ምን ይባላል፡፡ በእርግጥ ጽሁፉ 100% ትክክል ነው
ማለት ይከብዳል፡፡ ቆይቶም ማስተባበያ ሊወጣበት ይችላል፡፡ ፀሐፊውም ቢሆን ከመሬት ተነስቶ እንደዚህ አይነት ጠንካራ ነገር ይፅፋል
ማለትም ይከብዳል፡፡ የሆነው ሆኖ ፅሁፉን እንዳነበብኩት በተለያዩ ድህረ-ገፆች ላይ አቡነ ሳሙኤል ቀጣዩ የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ሆነው እንዲመረጡ በድብቅ(በህቡዕ)
ጫና የሚያደርግ አካል እንዳለ ያነበብኩት ትዝ አለኝ፡፡ እንዲያዉም በአንድ የማህበራዊ ድህረ ገጽ አቡነ ሳሙኤልን ጨምሮ የአምስቱንም
እጩ ተመራጮች ስም ዝርዝርና አሁን ያሉበትን ስልጣን አንብቢያለሁ፡፡ሆኖም ሁሉም በማህራዊ ድህረ ገፅ የተለቀቀው ሁሉ እውነት ነው
ብሎ መቀበል ስለሚከብድ ከምርጫው በኋላ የሚመጣውን ውጤት መጠበቅ ግድ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ የምርጫ ቅስቀሳ እያካሔዱ
መሆኑን ሳነብ ይህ በማህበራዊ ድህረ ገፆች ያነበብኩት ፅሁፍ ውሃ የሚያነሳ መስሎ ታዬኝ፡፡
በእርግጥም እኒህ
ሰው ይህን ተግባር ፈፅመው ከሆነ ህዝበ-ክርስቲያኑ በጣም እንደሚያሳዝኑ ጥርጥር የለውም፡፡ ክርስትና ራስን ዝቅ የሚያደርጉበት እንጂ
እኔ ስለምሻል ምረጡኝ የሚባልበት እምነት አይደለም፡፡ እንኳንስ በጳጳስ ደረጃ ያሉ ቀርቶ ገና ክርስትናን መማር የጀመሩ ሁሉ ይህን
ነገር ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ታዲያ እኒህ በጳጳስ ደረጃ ያሉ ሰው ምረጡኝ ብለው ዘመቻ መጀመራቸው ምን ፈልገው ነው? የሚል ጥያቄ
ማስነሳቱ አይቀርም፡፡ ይህ የምረጡኝ ዘመቻቸውን ሳነብ በእርግጠኛነት እንደማይመረጡ አውቅሁ፡፡ ይህን ስል ጠነቋይ ሆኜ አይደለም፡፡
ይልቁንም አንድ ክርስቲያን እኔ እበልጣለሁ ከሌላው የተሻልኩ ነኝ ካለ ተቀባይነት እንደማያገኝ ስለማውቅ ነው፡፡ ሆኖም ግን ግምቴ
ፉርሽ ሆኖ ከተመረጡ በህረተሠቡ ዘንድ ድብቅልቅ ያለ ስሜት መፈጠሩ የማይቀር ነው፡፡ እነዚህ በህብረተሠቡ ዘንድ ጥያቄ ሊያስነሡ
ይችላሉ ብዬ የምገምታቸውን ነጥቦች ለመጥቀስ እሞክራለሁ፡፡
የአቡነ ሳሙኤል
መመረጥና አለመመረጥ ከጥቂት ቀናት በኋላ የሚታወቅ ቢሆንም አሁን በምንሠማው ነገር የተለያዩ መላምቶች አሉኝ፡፡
የመጀመሪያው መላምቴ
እርሳቸው ከተመረጡ በህዝበ ክርስቲያኑ ተቀባይነት የማይኖራቸው እርሳቸው ብቻ ሳይሆኑ ድሮም በተወሠኑ ሰዎች በጥርጣሬ አይን የሚታዉ
አስመራጭ ኮሚቴውም ጭምር ነው፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለዉም እንደ አንድ ክርስቲያን ሳስበው መራጩ አካል ምረጡኝ ብሎ የሚዘምትን ጳጳስ
ሊመርጥ አይችልም የሚል ግምት በህብረተሰቡ ዘንድ መስረጹ አይቀርም፡፡ የምረጡኝ ዘመቻ ጀምረዋል የሚባሉት አቡነ ሳሙኤልም የአለማዊነት
ዝባሌን እያሳዩ ይገኛሉ፡፡ ምናልባትም በዚህ ከቀጠሉ የምርጫ ምልክታቸዉን ማሳወቃቸዉ አይቀርም፡፡ታዲህ በእምነታቸው
ጠንካራ የሆኑት መራጮች እነዚህን አባት ይመርጣሉ ተብሎ አይታሠብም፡፡ ነገር ግን የምርጫው ውጤት አቡነ ሳሙኤልን ለፓትርያርክነት
የሚያበቃ ከሆነ ህዝብ-ክርስቲያኑ በመረጩ አካልና በአስመራጭ ኮሚቴው ያለውን እምነት ዜሮ እንደሚያስገባው እያጠራጥርም፡፡ አልያም
ደግሞ በተለያዩ ድህረ ገፆች እንደሚፃፈው አቡነ ሳሙኤል ፓትርያርክ አድርጎ ለመሾም በህቡዕ ይንቀሳቀሳል የሚባለው አካል ስለመኖሩ
የሚወራውን ወሬ እውነትነቱን መቀበሉ ግድ ይሆናል፡፡ በቀላል አገላለፅ
ህብረተሠቡ ምርጫው ተጭበርብሯል ወደ ሚለው ማመዘኑ ሳይታለም የተፈታ
ይሆናል፡፡ ባጠቃላይ ምዕመኑ በቤተ-ክርስቲያኒቱ አስተዳዳሪዎች ላይ ያላቸውን እምነት እንደሚቀንሱ እያጠራጥርም፡፡ ይህ ደግሞ በጣም
አሳፋሪ እና ቤተ ክርስቲያንቱ የቆመችለትን አላማ እንደረሳች ይቆጠራል፡፡ሌላኛው የምዕመኑ
ስጋት ሊሆን የሚችው ነገር ደግሞ በትክክለኛ አቡነ ሳሙኤል ቢመረጡም እንኳን ቤተ-ክርቲያኒቱን እርሳቸው በደንብ ሊመሯት አይችሉም
የሚል ይሆናል፡፡ በፅሁፍ እንዳነበብነው ከሆነ በምረጡኝ ዘመቻቸው ብዙ ገንዘብ እንዳፈሠሱና ወደፊትም የውጭ እድል እንደሚፈቅዱላቸው ቃል የገቡላቸዉ ሰዎች እንደሚኖሩ ነው፡፡ ለስልጣን ይህን
ያህል የሚጉዋጉ ከሆነ ስልጣን ከያዙ በኋላም ለቤተ-ክርስቲያኗ ሳይሆን ዉለታ ለመመለስ ብዙ ወጭ ማፍሰሳቸዉ እንደማይቀር መጠርጠሩ
ተገቢ ነዉ፡፡በዚህም
ምክንያት ምእመኑን ለመንግስተ ሰማያት የማዘጋጀት ተልእኮ ያላት ቤተ ክርስቲያን ስራዋ ሁሉ አለማዊ
አጀንዳን ማራገቢያ ሊትሆን የማትችልበት ምንም ምክንያት አይኖርም፡፡ ቤተ-ስርቲያኒቱ ውስጥም ሙስና እንደፈለገ ሲፈነጭበት ማየት
እንደማይቀር መገመት ቀላል ነዉ፡፡
እንደ እኔ መላምት
ጥያቄ ሊያስነሳ የሚለችው የአቡነ ሳሙኤል መመረጥ ብቻ ላይሆን ይችላል፡፡ አለመመረጣቸውም በተወሠኑ ዘንድ ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም፡፡
ከተለያዩ ድህረ
ገፆች እንደሚገለጸዉ አቡነ ሳሙኤል በምርጫ ዙሪያ ከመነሳታቸው በፊት ይህ እርሳቸውን ሊያስመርጥ በህቡዕ ይንቀሳቀሳል የተባለው አካል
በመጀመሪያ ሊያስመርጥ ነው ተብሎ የተወራው እርሳቸውን ሳይሆን ሌላ በእራኤል አገር የሚገኙ አባትን እንደሆነ ነበር፡፡
እኒህ በእስራኤል
ሃገር የሚገኙ አባት ከተመረጡም ጥያቄው በተመሳሳይ ይነሳል፡፡ ጥያቄ የሚያስነሳውም ሰሞኑን አቡነ ሳሙኤል የምርጫ ዘመቻ የመጀመራቸውን
ወሬ ያስነሳው ድብቅ አካል እንደሚኖር ነው፡፡ ህብረተሠቡ ካነበበውና ከሠማው ተነስቶ በእራኤል የሚገኙትን አባት መሾምና አለመሾም
የሚጠባበቅ ከሆነ ይህ የአቡነ ሳሙኤልን ጉዳይ ይዞ የተነሳ ድብቅ አካል የህብረተሠቡን አቴንሽን ከእስራኤሉ አባት ወደ አቡነ ሳሙኤል
እንዳዞረዉ መጠርጠሩ አይቀርም፡፡ ስለዚህ በድንገት የእስራኤሉ አባትም ከተሾሙ ምእመኑ በአስመራጭ ኮሚቴዉና በመራጮች የሚኖረዉ እምነት
ዝቅተኛ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡
ሌላኛው መላምቴ
ደግሞ ይህ የአቡነ ሳሙኤልን የምረጡኝ ዘመቻ መጀመራቸዉን መረጃ የሰጠዉ ሰዉ(አካል) ሆን ብሎ አቡነ ሳሙኤል እንዳይመረጡ የሚፈልግ
ሊሆንም ይችላል፡፡ይህን ተግባር የሚፈጽመዉ አካል(ሰዉ) በጭፍን ጥላቻ አልያም ደግሞ አቡነ ሳሙኤል ለቤተ
ክርስቲያን ስለማይመጥኑ መመረጥ የለባቸዉም የሚል አቁዋም ሊኖረዉ ይችላል፡፡ይህ አቁዋሙ ፍሬ እንዲያፈራ ደግሞ የአቡነ ሳሙኤልን
ተቀባይነት ባገኘዉ ሁሉ አጋጣሚ ማሳጣት ይኖርበታል፡፡ከነዚህ ዘዴዎች ዉስጥ ይህ የምረጡኝ ዘመቻቸዉን የሚናገር መረጃ ለህብረተሰቡ
ማድረስ አንዱ ሊሆን ይችላል ብሎ መገመቱ ተገቢ ነዉ፡፡እኒህ አባት ከጥቂት አመታት በፊት ከቀድሞዉ ፓትርያርክ አቡነ ጳዉሎስ
ጋር እርስ በርሳቸዉ ሲወጋገዙ እንደነበር ይታወቃል፡፡ምናልባትም በወቅቱ የነበሩት የህትመት ዉጤቶች ያስነብቡት እንደነበረዉ ከሆነ
አቡነ ሳሙኤል ቅዳሴ በኢንተርኔት ቢሆን ችግር የለዉም የሚል እምነት እንዳላቸዉ አቡነ ጳዉሎስ
ሲያወግዙ በተቃራኒዉ ደግሞ አቡነ ጳዉሎስ ታቦተ ጽዮንን አሜሪካ ለጉብኝት ሊልኩዋቸዉ
ነዉ ሲሉ አቡነ ሳሙኤል አቡነ ጳዉሎስን ያወግዙዋቸዉ እንደነበር ሲገለጽ ነበር፡፡ይህን
ያስታወሰ ሰዉ አቡነ ሳሙኤል እንዲመረጡ ላይፈልግ ስለሚችል ይህን የአሁኑን የምርጫ ቅስቀሳ መረጃ ሊያስተላልፍ ይችላል፡፡በመሆኑም
አቡነ ሳሙኤል የምረጡኝ ዘመቻ ላያካሂዱም ይችላሉ ብሎ ማሰብ ተገቢ ነዉ፡፡እዉነት የምረጡኝ ዘመቻ አካሂደዉ ከሆነ ግን በጣም የሚያሳዝንና
ከክርስትና ስርዓት ዉጭ የሆነ ተግባር እንደፈጸሙ ይሰመኛል፡፡ለመላምቶቻችን ፍንጭ ከጥቂት ቀናት በሁዋላ እንደምናገኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
እሺ ማንን እንመን?
አቡነ
ሳሙኤል የምረጡኝ ዘመቻ ጀምረዋል መባላቸዉ ለጽሁፌ መነሻ ቢሆነኝም በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ግራ መጋባት ከጀመርኩ ሰነባብቻለሁ፡፡በተለይም
ደግሞ በዉጭ ሀገር የሚገኙ አባቶችና የሀገር ዉስጥ አባቶች እርስ በርሳቸዉ ሲወጋገዙ ስሰማ በጣም ነዉ የማዝነዉ፡፡ይህን ጽሁፍ እየጻፍኩ
እያለ እንኩዋ የሀገር ዉስጥ ሲኖዶስ ለጋዜጠኞች የሰጠዉን ጋዜጣዊ መግለጫና በዉጭ ሀገር ያለዉ ሲኖዶስ ተወካይ ለአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ
የሰጠዉን ምላሽ በሸገር በኩል እየሰማሁ ነበር፡፡በሀገር ዉስጥ ያለዉ ሲኖዶስ አቡነ ማርቆርዮስ ስላመማቸዉና በራሳቸዉ ፈቃድ ስለለቀቁ
እንጅ በእርሳቸዉ ላይ ሌላ ጳጳስ እንዳልተሾመባቸዉ ለጋዜጠኞች ሲገልጹ በአንፃሩ ደግሞ በአሜሪካ የሚገኙት
አባቶች አቡነ ማርቆርዮስን የቀድሞዉ ጠቅላይ ሚንስትር ታምራት ላይኔ እንዳባረራቸዉና በላያቸዉ ላይ ሌላ ጳጳስ እንደተሾመባቸዉ
ማስረጃም እንዳላቸዉ እየተናገሩ ነበር፡፡ከዚሁ ጋር አያይዘዉም ለሰላም ድርድሩ አለመሳካት የሀገር ዉስጥ አባቶችን
ተጠያቂ አድርገዋል፡፡ይህንም ሲያጠናክሩ የሀገር ዉስጥ ተወካዮች ለሀገር ዉጭ አባቶች የመኖሪያ ፍቃድ እንደሚያሰጡዋቸዉ እንጅ አቡነ
ማርቆርዮስ ወደ ቀደመዉ ስልጣናቸዉ እንዲመለሱ ፍላጎት እንደሌላቸዉ አክለዋል፡፡ታዲያ በዚህ መሀል ማንን እንመን? እዚህ ያሉት እኛ
ነን ትክክል ዉጭ ያሉትም እና ነን ትክክል ይላሉ፡፡ከሁለቱም ጎን እኛ ነን ትክክል ቢሉም እዉነቱ ግን አንዱ ብቻ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ታዲያ
ስህተት የሆነዉ አካል ስህተቱን አለማመኑ ምን ማለት ነዉ? ይቅር መባባል እየተረሳ ነዉ ማለት ይቻላል፡፡በምእመኑ ዘንድ ተቀባይነትም
የሚያገኙት ይቅርታን በሚያስቀድሙ ላይ ነበር፡፡ እንዳስተማሩንም ይቅርታ የሚጠይቅ የበደለ ብቻ ሳይሆን የተበደለም ነዉ፡፡ምን ያደርጋል
ቲዎሪ ብቻ ሆኖ ቀረ እንጅ፡፡ክርክራቸዉ ሁሉ አንዱ አንዱን የማዉገዝ ዘመቻ ብቻ ሆኖብኛል፡፡ይህ ደግሞ የሁለቱን ዉዝግብ ፖለቲካ
እያስመሰለዉ ይገኛል ፡፡እንዲያዉም እንደሰማሁት ከሆነ ኢ.ቴ.ቪ በዉጭ ሀገር በሚገኙ አባቶች ላይ ዶክመንታሪ ፊልም እየሰራ ነዉ፡፡ይህ
ደግሞ የለየለት ፖለቲካ ነዉ፡፡ እዉነቱ የት እንዳለ እነርሱ የሚያዉቁት ቢሆንም ህብረተሰቡ ግራ በመጋባትና በአባቶች ላይ ጥርጣሬ
ማሳደሩ የማይቀር መሆኑ ያሳዝናል፡፡ እዉነት ለመናገር የሌላዉን ባላዉቅም እኔ በቤተ ክርስቲያን አባቶች ላይ ያለኝ እምነት እየቀነሰ
ነዉ ሁሉንም አባቶች ባይሆንም፡፡
እግዚአብሔር ለሀይማኖት ሙዋች አባት ይስጠን!!!
No comments:
Post a Comment