Friday, February 15, 2013

የጎጃም አርሶ አደሮችን የቅጣት ዉርስ (ሌጋሲ)ማን ይፋቀዉ?

የአባት እዳ ለልጅ ይባል ነበር ድሮ
    ባያት እዳ ገባሁ እኔማ ዘንድሮ
የግጥሙን ወርቅ ለጊዜዉ እንተወዉና ሰሙን ብቻ ይዘን እንቀጥል::
እንደ መነሻ:በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ አንድ ትምህርት አለ::በመጽሃፍ ቅዱስ  ኦሪት ዘፍጥረት(Genesis) ላይ እንደተጻፈዉና የቤተ ክርስቲያን አበዉ ሊቃዉንት እንዳስተማሩን እግዚአብሔር አምላክ አዳምን ከፈጠረዉ በሁዋላ በኤደን ገነት አኖረዉ:: የህይወትንም ዛፍ እንዲበላ ፈቀደለት::ሰዉ ብቻዉን ይኖር ዘንድ መልካም አይደለምና የህይወት አጋር የምትሆነዉን ከግራ የጎን አጥንቱ ወስዶ ሄዋንን(የህያዋን እናት) ፈጠረለት::አዳምና ሄዋን በገነት እየኖሩ ሳለ እግዚአብሔር አንድ ትዕዛዝ ሰጥቶዋቸዉ ነበር::ይህም ክፉዉንና ደጉን የሚያሳዉቀዉን እጸ በለስን እንዳይበሉ ነበር::በእባብ አሳሳችነት ሄዋን እንዳይበሉ የታዘዙትን እጽ በላች ለአዳምም ሰጠችዉ::እነሆ እግዚአብሔርም አዳምን ከገነት አስወጣዉ እንዳይበሉ የታዘዙትን ዕጽ በልተዋልና::ጥሮ ግሮ እንዲበላም  እግዚአብሔር ፈረደበት::የአዳም ሀጢያትም ለልጅ ልጁ ሁሉ ይተላለፍ ነበር::ነገር ግን እግዚአብሔር አዳም ከገነት ተባሮ ይቀር ዘንድ አልወደደም::ለአዳምም ቃል ገባለት::”ከልጅ ልጅህ ተወልጀ ነፃ አወጣሀለሁአለዉ::ቃል የገባለትንም ፈፀመለት::ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ አዳምን ከሃጢያቱ አዳነዉ::አዳም ነፃ ወጣ::ለልጅ ልጅ ይተላለፍ የነበረዉም የሀጢያት ዉርስ (ጥንተ አብሶ) ተደመሰሰ::”እግዚአብሄር የአዳምን የእዳ ደብዳቤ ቀደደለትተብሎ እንደተፃፈዉ::
እግዚአብሔር አዳምን ከልጅ ልጁ ተወልዶ ባያድነዉ ኖሮ የአዳም የልጅ ልጆች ባልሰሩት ጥፋት(ዕፀ በለስን ሳይበሉ) ሀጢያተኛ ይባሉ ነበር::መልካም እየሰሩ ቢኖሩም መጨረሻቸዉ መንግስተ ሰማያት ሳይሆንገሃነበ እሳትይሆን ነበር::አሁን ግን እግዚአብሔር አድኑዋቸዋል::ይህ ቃል ኪዳን ከተፈጸመ ከ2000 ዓመታት በላይ ሆኖታል::አሁን ባለንበት ዘመን ኢህአዴግ ሀገሪቱዋን መምራት ከጀመረ ወዲህ በጎጃም አርሶ አደሮች ላይ እየተካሄደ ያለዉን ከአያት ወደ አባት ከዚያም ወደ ልጅና የልጅልጅ እያለ የሚቀጥለዉን አድሎአዊ የመሬት ክፍፍልና ዉርስ ሳይ ይህን 2000 ዓመታት በፊት የተፈጸመ ታሪክ እንዳስታዉስ አድርጎኛል::ታሪክ እንደሚነግረን በፊዉዳሉ  ዘመን ስርዓቱን ከተቃወሙት ክፍሎች መካከል የጎጃምና ባሌ አርሶ አደሮች ይገኙበታል:: አሁንም በጎጃም አርሶ አደሮች ላይ እየተደረገ ያለዉ አድሎአዊ የመሬት ክፍፍል አርሶ አደሮችን ለአመጽ የሚቀሰቅስ ነዉ::የዚህ አድሎአዊ አሰራር ገፈታ ቀማሽ የሆኑት አርሶ አደሮች በደርግ ጊዜ ስልጣን ነበራችሁ የሚባሉ ወገኖች ናቸዉ::እነዚህ ወገኖች በደርግ ጊዜ ያላግባብ መሬት ይዛችሁ ቆይታችሁዋል በሚል ሰበብ አሁን እንዲተዳደሩበት እጃቸዉ ላይ የቀረዉ ከሌላም ማህበረሰብ እጅግ ያነሰ ነዉ::በአንጻሩ ደግሞ የአሁኑ መንግስት ሹማምንት በራሳቸዉ ስም ይቅርና ገና በ5 አመት ልጃቸዉ ስም መሬት አላቸዉ:: መንግስታችንን 40 ዓመት ይንገሱ ብለን ከተዉን ደግሞ  መቼም ሼም የሚባል አልፈጠረባቸዉምና ገና በተረገዙ ልጆች ስምም መሬት ሊቀራመቱ ይችላሉ:: ይህ ሁኔታም የሚያመለክተዉ ብአዴን/ኢህአዴግ የሚመራዉ መንግስት በእነዚህ ወገኖቻችን ላይ የበቀል ጅራፉን እያሳረፈባቸዉ መሆኑን ነዉ::ምናልባትም እንደተባለዉ እነዚህ ወገኖች በደርግ ጊዜ ስልጣናቸዉን ተጠቅመዉ ከሌላዉ ማህበረሰብ የበለጠ መሬት ይዘዉ ከተገኙ ትርፉን መሬት ብቻ መንጠቅ እየተቻለ ገና ለገና በደርግ ጊዜ ስልጣን ነበራችሁና እንደሌላዉ መብላት አትችሉም ማለት ግልጽ የሆነ -ሰብአዊ ድርጊት መሆኑን ነጋሪ አያስፈልገዉም::በዚህም ምክንያት እነዚሀ ቢሮክራሲዎች የሚባሉት የሌላ ሰዉ መሬት በመከራየት ነፍሳቸዉን ለማሳደር ሲንገላቱ ሲታዩ እጅግ በጣም ያሳዝናሉ::ይህን ሁሉ የሚያደርገዉ ደግሞ ክቡር አቶ አያሌዉ ጎበዜ የሚመሩት የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ነዉ::በዝርዝር ባይሆንም ከዚሁ - ሰብአዊ ድርጊት ይቆጠቡ ዘንድ የኛ ፕሬስጋዜጣ ላይ ለአቶ አያሌዉ ጎበዜ የተጻፈ ማመልከቻ አንብቢያለሁ::በየኛ ፕሬሰ ጋዜጣ የተጻፈዉ ነገር ትክክል ስለመሆኑ እኔም ምስክር እሆናለሁ::ይህን ጉዳይ መጠየቅ የጀመርኩት ዛሬ በጽሁፌ አይደለም::ምንም እንኩዋ በተሰጠኝ መልስ ባልደሰትም ከሁለት አመት በፊት አዳማ ከተማ ዉስጥ አንድን የኢህአዴግ ባለስልጣን ጠይቄዉ ነበር::ነገር ግን ጉዳዩ የክልሉ መንግስት እንደሆነ ከመጥቀስ ዉጭ ይህ ነዉ የሚባል አጥጋቢ መልስ አልሰጠኝም ነበር::እንዲያዉነጋዴ ስንቁ ስለተቀማ ሳይሆን የጉዋደኛዉ ስለቀረ ነዉ የሚቆጨዉአይነት አይሁንብኝና ይህ ቢሮክራሲ እያሉ መሬትን ነጥቆ ባዶ እጅን የማስቀረት ተግባር የሚካሄደዉ በአማራ ክልል ጎጃም ዉስጥ መሆኑ ደግሞ በጣም ይገርማል::እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ነገር ጎጃም ላይ የሚደረገዉ የመሬት ንጥቂያ ለምን በሌሎች የሀገራችን ክፍሎች ላይስ አይተገበርም? እያልኩ እንዳልሆነ ነዉ::ይህን የምመኝ ከሆነማ ግልጽ የሆነ ምቀኝነት ይሆንብኛል::”ትዉልድ ይዳን ትምህርት በኛ ይብቃእንዲሉ የአሁን ዘመን ተማሪዎች የስቃይ ስቃይማ እዚያዉ ጎጃም ብቻ ይበቃል::ሆኖም ግን ይህ ተግባር የሚከናወነዉ ጎጃም ላይ ብቻ መሆኑ ጥያቄዎችን በበለጠ እንድናነሳ ያደርገናል::በፊት ይህ ተግባር ጎጃም ላይ እንደሚካሄድ የፌዴራል መንግስት የሚያዉቅ አይመስለኝም ነበር::ሆኖም ግን አዳማ ላይ ስለጉዳዩ ጥያቄ ያነሳሁለት የኢህአዴግ ተወካይ የሌላ ክልል ተወካይ መሆኑና ጉዳዩን እንደሚያዉቅ ሲመልስልኝ በፌዴራል ደረጃም እንደሚታወቅ ተገንዝቢያለሁ::ለክልሉ ህዝብ ቆሚያለሁ የሚለዉ ብአዴንና ለአርሶ አደሩ ጥብቅና እንደሚቆም የሚናገረዉ ኢህአዴግም ራሳቸዉ አርሶ አደሮችን መሬታቸዉን ነጥቆ በራብ አለንጋ ሲቀጣቸዉ ሲታይ እዉነት ይህ ድርጅት ነዉ ህዝብን የሚወክል? ያስብላል::ብአዴን ሆይ በዉኑ የወከሉህ ሰዎች ለልጆቻቸዉ የሚሰጡት አጥተዉ በራብ ሲሰቃዩ ማየት  ያስደስተሃልን!?ብአዴን የተዋጋዉ አንድም አድሎአዊ አሰራርን በመቃወም ነበር::ታድያ እርሱ ጠልቶት ለብዙ አመታት የተዋጋዉን አድሎአዊ አሰራር በሌሎች ላይ ሲተገብረዉ ለምን ሀፍረት እንደማይዘዉ አይገባኝም::ይህ የሚጠቀሙበትን መሬት መቀነስ በአባቶች ብቻ የሚያበቃ አይደለም::ልጆችም ብዙዉን ጊዜ ይህን እጅግ አነስተኛ የሆነ የአባታቸዉን መሬት ይዘዉ ነዉ የሚቀጥሉት::በመግቢያየየአባት እዳ ለልጅ” ያልኩትም ለዚሁ ነዉ::ልጆች ምንም በማያዉቁት ጉዳይ የቅጣቱ ተቁዋዳሽ ይሆናሉ::በዘመነ ኢህአዴግ የተወለዱትን ልጆች አባታቸዉ የደርግ ባለስልጣን ነበር ብሎ መቅጣት ምን ይሉታል? ክቡር አቶ አያሌዉ ጎበዜ ሆይ እስኪ ያስቡት የእርስዎ ልጆች እንኩዋንስ የሚበሉት አጥተዉ ለአንድ ቀን እንኩዋ ያለመኪና በእግራቸዉ ትምህርት ቤት ይሂዱ ቢባሉ የሚሰማዎትን ስሜት::የአቶ አያሌዉ ድርጅት አንድ ቀን ከስልጣል ቢወርድና አይናቸዉ እያየ ጆሮዋቸዉም እየሰማ እርስዎ ሰዉን ቢሮክራሲ እያሉ ሲበድሉ ነበርና ቤትዎንና ያፈሩትን ሀብት ተነጥቆ ልጆቻችሁ ከደጅ ይፍሰሱ ቢባሉ አቶ አያሌዉ ምን አይነት ስሜት እንደሚሰማቸዉ አላዉቅም:: ይህ የበቀል እርምጃ ከአሁኑ የማይቆም ከሆነ የወደፊት የእነ አቶ አያሌዉ ጎበዜ እጣ ፈንታም ከዚሁ የተለየ አይሆንም:: እነርሱ እንደሚሉት ከ40 ዓመት በሁዋላ ቢሆንም ስልጣን መልቀቃቸዉ መቼም አይቀሬ ነዉ::ነገር ግን ይህ አይነት የበቀል እርምጃ ካሁኑ ሊቆም ይገባል::”በራስህ ላይ እንዲደረግ የማትፈልገዉን ነገር በሌሎች ላይ አታድርግይባላልና አሁንም ቢሆን የተከበሩ አቶ አያሌዉ ይህን የሰሩትን የታሪክ ስህተት ሊያስቡበትና ሊያስተካክሉት ይገባል እላለሁ:: ቅሬታ ሰምቶ ጆሮ ዳባ ልበስ ማለት ለኢህአዴግ ብርቅ እንዳልሆነ እናዉቃለን::ታዲያ እነ አቶ አያሌዉ አሁንም ይህን ነገር ችላ ካሉት ሌላ ማን ያስቀረዉ? የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነዉ::ምናልባትም እግዚአብሔር አዳምን ከልጅ ልጁ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ እንዳዳነዉ ሁሉ ከቢሮክራሲዎችም የልጅ ልጅ ተወልዶ አባቶቹን እና አያቶቹን የቅጣት ዉርስ(ሌጋሲ) የሚፍቅ ጀግና የሚነሳበት ሩቅ ላይሆን ይችላል::ይህ ይሆን ዘንድም ምኞቴ ነዉ::የነገ ሀገር ተረካቢ ህጻናት በአባታቸዉ እዳ ሲቀጡ መኖር ሊቆም ይገባል እላለሁ:: ገና በአፍላ እድሜያቸዉ በጭንቅላታቸዉ የሚሰርጽ በቀል እንጅ ሌላ አይደለም::እነዚህ ልጆች ለሀገራቸዉ መልካም ነገርን ያስባሉ ማለት ዘበት ነዉ:: ለሀገራችን ጥሩ የምንመኝላት እርሱዋም ለኛ ጥሩ ስትሆን ነዉ::”ሀገሬ ምን ሰራችልኝ ሳይሆን እኔ ለሀገሬ ምን ሰራሁላትበሉ የሚለዉን ፍልስፍና በበኩሌ አልቀበለዉም::ሀገሬ ጥሩ ነገር ካልሰራችልኝ ምኑ ላይ ነዉ ሀገርነቱዋ?የስቃይ ኑሮማ ሌላ ሀገር ብሄድም ቢያንስ በስደተኛነት ልኖር እችላለሁ:: እናም

   እንደ አንተ ያለ የቸገረ ለት
    አልወለደችም ወይ የጎጃም እናት
ብላ እንዳዜመችዉ አርቲስቱዋ እዉነትም እንዲህ ያለ ግፍ ሲሰራ መፍትሄ የሚፈልግ ወንድ የሚያስፈልግ ይመስለኛል::ይህ አድሎአዊ አሰራር ይቀር ዘንድ ተጎጂዎች ብቻ ሳይሆኑ  ሰብአዊነት የሚሰማዉ ሰዉ ሁሉ መጠየቅ አለበት:: በእርግጥ የአርሶ አደሩ ችግር ይህ ብቻ አይደለም::አንድ ለኢትዮጵያ የሆነዉ ኢ.ቴ.ቪ ሁሌም የአርሶ አደሩን እድገት ቢያቀነቅንም እዉነታዉ ግን ሌላ ነዉ::በተፈጥሮ ጥበቃ አርሶ አደሩ ያለዉ ተነሳሽነት ሁልጊዜ ቢተረትልንም እዉነታዉ ግን አርሶ አደሩ ለተፈጥሮ ጥበቃ ስራ የሚወጣዉ “ብር ትቀጣላችሁ”የሚለዉን የካድሬዎች ማስጠንቀቂያ በመፍራት ነዉ::የአርሶ አደሩ ችግር ተዘርዝሮ የማያልቅ ቢሆንም መንግስታችን የምግብ እንጅ የዲሞክራሲና ነጻነት መብት ጥያቄን መልሰን ችሎቱን ዘግተናል ብሎ ስላወጀብን የምግብ ምንጭ የሆነዉን የአርሶ አደሩን አድሎአዊ የመሬት ክፍፍል ላይ ያለኝን እይታ ጠቅሻለሁ::
 ሰብአዊነት የሚሰማዉ አስተዳደር ይስጠን!!!

1 comment:

  1. it is the history of me & my families at east gojjam lumame . so we must collaborate to remove such traditional beliefs

    ReplyDelete