Wednesday, February 13, 2013

የወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ ፈራጅ ነኝ ማለት ለጥብቅና ወይስ ለጽድቅ?

ጋዜጣ ማንበብ እወዳለሁ፡፡ ከሚያስጠሉኝ ቀናት ውስጥ ደግሞ ሰኞ እና ሐሙስ በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ ለምን ብትሉኝ በእነዚህ ቀናት ጋዜጣ ስለማይታተም ነው፡፡ በእርግጥ ከብርብ ጊዜ ወዲህ አርብናም ከነዚህ ከሚያስጠሉኝ ቀናት አንዷ ሆናለች፡፡ (የስፖርት ጋዜጣ ስለማለነበት ማለት ነው)፡፡ ዛሬ ሕንን ጽሁፍ እንድጽፍ ያነሳሳኝ በእለተ ማክሰኞ ከሚታተሙ ጋዜጦች ውስጥ በየኛ ፕሬስ ጋዜጣ ነሐሴ 15 ቀን 2004 ዓ/ም እትም ላይ ከወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ ጋር የተደረገውን ቃለ ምልልስ ካነበብኩ በኋላ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ጋዜጦቼን አንብቤ የማልስማማባቸውንም ሀሳቦች “ሰምቶ እንዳልሰማ” ከማለፍ ውጭ ሌላ አማራጭ አልነበረኝም:: ይህንንም የመረጥኩበት ምክንያት ብጽፍም ምን ለውጥ አመጣለሁ በማለት እና መልስ የመስጠት ችሎታ ስለሌለኝ ነው፡፡ ይህ ውሳኔየ ግን ሊቀጥል አልቻለም፡፡ የፈለገው ችሎታ ባይኖረኝ እና ለውጥ ባላመጣም የግል ሀሳቤን ለመሰንዘር ውስጤ አነሳሳኝ:: ላለመፃፍ ስወስንም መረበሽ ጀመርኩ:: እነሆ እንደ ክርስቲያንነቴ በቃለ ምልልስ ውስጥ ያሉ ሀሳቦች ብዙዎቹን ስለማልስማማባቸው የእኔን ሀሳብ ለማሳንት አሀዱ ብዬ ጀምሬለሁ፡፡
      እንደ መነሻ
      ከዚህ በፊት ስለ ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ የተወሰነ ነገር በወሬ ደረጃ እሰማ ነበር፡፡ የተወሰኑት ወ/ሮ እጅጋየሁ ለቤተ ክርስቲያ በጣም ተቆርቋሪ እንደሆኑ ሲናገሩ ሌሎች ደግሞ ለለሰብ ና የቆ ለቤተ ክርስቲያ ተቆርቋሪ እንዳልሆኑ ናገራሉ፡፡ በቅርቡም “በሃይማኖት ሽፋን እስከመቼ” የሚል መጽሐፍ እንዳሳተሙ አውቃለሁ፡፡ መጽሐፉንም ከዛሬ ነገ አነበዋለሁ ስል ይኸው ዛሬ ድረስ ሳላነበው ቀረሁ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ነው እንግዲህ የወ/ሮ እጅጋየሁን ቃለ ምልልስ በየኛ ፕሬስ ጋዜጣ ያነበብኩት በእርግጥ ይህንን ጽሁፍ ስጽፍ ከመፅሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እየጠቀስኩት ለመመለስ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀቱ ስሌለኝ ነው፡፡ እንደ ክርስያንነቴ መጽሐፍ ቅዱስን ጠንቅቄ ማወቅ ቢጠበቅብኝም ሳላደርገው መቅረቴ የእኔ ጥፋት ነው፡፡ ይህም በመሆኑ አብዛኛው ጽሁፌ መልስ ከመስጠት ይልቅ ጥያቄ ላይ ያነጣጥራል፡፡
ወደ ጥያቄዎቼ
ወ/ሮ እጅጋየሁ መጽሁፍን ማነው ያሳተመው (በሃይማኖት ሽፋን እስከመቼ) የሚለውን ተብለው ሲጠየቁ በግላቸው እንዳሳተሙት ከተናገሩ በኋላ በመፅሐፉ ይቅርታ የሚጠይቁት ሰው እንደሌለ አክለውበታል፡፡ የመጽሐፉን አሳታሚ ለተጠየቀ ሰው ይቅርታ የምጠይቀው ሰው የለም የሚል መልስ አራምባና ቆቦ ቢሆንም ዋናው ጥያቄየ ግን ይቅርታ መጠየቅ ሃጢያቱ ምንድነው ነው የሚል ነዉ:: ወ/ሮ እጅጋየሁ እነሆ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሆኖ የበደሉትን “የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” እንዳለ ዘነጉት እንዴ? ሌላም ጥያቄ ልጨምርልዎት መቼም የዘውትር ጸሎትን አያነቡም ወይም በቃልዎ አያዉቅቱም ብየ መገመት ለእርስዎ ያለኝን ክብር መቀነስ ይሆንብኛልና እንደዚህ ብዬ አልገምትም፡፡ ታዲያ በዘወትር ጸሎት ላይ (አባታችን ሆይ…) “እኛም የበደሉንን ይቅር እንድንል…” የሚለውን አያውቁትም? ሰዎች ቢበድሉዎት እንኳን የበደልዎት ይቅርታ መጠየቅ ታላቅነት አይመስልዎትም ? እዚህ ላይ በእርግጥ ይቅርታ ላለመጠየቅ የወሰኑበት ምክንያት አስተዳደግዎ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም በቃለ ምልልስዎ እንደጠቀሱት “አትጣይ ግን ተደብድበሽ አትምጪ ካሳ ብከፍል ይሻለኛ” እየተባሉ እንዳደጉ ገልፀውልናል፡፡ ታዲያ ይህ ያልሸነፍም ባይነት አስተዳደግዎ ይቅርታ መጠየቅ ታናሽነት ነው የሚል ስሜት አላስተማረዎትም?
      ሌላው ወ/ሮ እጅጋየሁ የተጠየቁት ጥያቄ እግዚአብሔር አምላክ ነፍሳቸውን ይማርና በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ላይ ስለተነሱ ተቃውሞች እና በቀጨኔ መድኃኔአለም ቤተ ክርስቲያን ጫማ እንድተወረወረባቸውና ለዚህም ምክንያቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ነው፡፡ ሲመልሱም ችግሩ የዘር ነው ብለዋል፡፡ እዚህ ላይ ዘር የሚለው ትርጉም ስላልገባኝ ነው፡፡ እኔ ዘር እስከሚገባኝ ድረስ ሁሉም ሰው የአዳምና ሄዋን ዘር ነው፡፡ ወ/ሮ እጅጋየሁ የትግራይ፣ የአማራ፣ የኦሮሞ ወዘተ… ዘር የሚባል አለወይ ብየ ልተይቅዎት ዕስኪ ካለስ ማነው እንዲህ ብሎ የከፈለው? በፖለቲካም እኮ የትግራይ፣ የአማራ፣ የኦሮሞ ወዘተ… ብሔር እንጂ ዘር አይባልም፡፡ እንኳስ በሃይማኖት:: እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ጉዳይ ጫማ ወርዋሪውን እየደገፍኩ አይደለም፡፡ እንኳን በብፁዕ አባታችን ቀርቶ በሌላም ሰው ቢሆን ተቃውሞውን በጥያቄ እንጂ በሃይል ለመግለጽ መሞከር ከነውሮች ሁሉ የከፋ ነውር ነው፡፡ የእኔ ጥያቄ ግን በክፍት የመጣን በቀና ካልመለሱት ክርስትናው ምኑ ላይ ነው የሚለው ነው፡፡
      ሌላው በጣም የገረመኝ ነገር ባህታዊ ሰው አይሳደብም ብለዋል፡፡ እኔም እስማማበታለሁ፡፡ ወ/ሮ እጅጋየሁ ግን እርስዎ በመልስዎ ላይ “እንደ ፌንጣ እየዘለለ ባሕታዊ ነኝ እያለ…፣ ዱርዬ” የመሳሰሉትን ቃላት ሲጠቀሙ ስድብ አይመስልዎትም ? በዚህ ስንቀጥል እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ባህታዊ ነኝ ባዩ አቡነ ጳውሎስን በሰይፍ ሊገድላቸው “ገዳይ” እያለ እየፎከረ እንደመጣና አባታችንም “ተወኝ” እንዳሉት ጠቅሰዋል፡፡ ታዲያ አባታችን ተወኝ ከማለት ውጪ ሌላ የመከላከል እርምጃ እንዲወስዱ እንጠብቅ? ዓለምን ለናቀ እንደ መስዋእትነት ታላቅ ጽድቅ የት አለ? ወ/ሮ እጅጋየሁ እርስዎ መሳሪያ ቢይዙ ባህታዊውን ይገድሉት እንደነበረ ጠቅሰውልናል፡፡ እንደእኔ ሃሳብ “ፈጣሪም እውቆ ሰማይ አርቆ” እንደሚባለው እንኳንም መሳሪያ አልያዙ፡፡ እንደ እርስዎ በሃማኖቱ የገፉት ሰዎች እንደዚህ ካሉ ለትውልዱ ምን መልእክት ነው የሚያስተላልፉት? “ግራህን በ    ጥፊ ለሚመታህ ቀኝህን ስጠው” የሚለው ሃይማኖታዊ ቃል የትነው የሚሰራው?
      አሁንም እንቀጥል አቡነ ጳውሎስ ሽጉጥ ይይዛሉ ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ ደግሞ ሽጉጥ መያዝ ችግር እንደሌለው ሲመልሱ በጣም ግራ  ገብቶኛል፡፡ በእርግጥ አቡነ ጳውሎስ ሽጉጥ ይይዛሉ ብለው ሺህ ጊዜ ቢነገሩኝ አላምንም፡፡ ባይኔ ባይም የእይታ ችግር እንዳለብኝ ነው የምረዳው ሆኖም ወደ ወ/ሮ እጅጋየሁ ጥያቄና መልስ ስመጣ አይበለውና አቡነ ጳውሎስ ሽጉጥ ቢይዙ ችግር እንደሌለው ነው የነገሩን፡፡ ወ/ሮ እጅጋየሁ የእኔ ጥያቄ ሽጉጥ የሚይዙት ምን ሊያደረጉት ነው? ይህቺን ዓለም ንቆ በመንፈሳዊ ሕይወቱ የበረታ፣ በእግዚአብሔር ሙሉ እምነቱን የጣለ ሰው በሥጋ ስለመቆየት ያስባሉ ወይ? እራስን መከላከል የምትለዋን ቃል ለዓለማውያን እንጅ ለመንፈሳውያን ጭራሽ አይጠቅምም፡፡ ለፃድቅ ሰው በሥጋ ከመቆየት ይልቅ ወደ አባቱና ሁሉም ወደ ሚናፍቀው መንግስተ ሰማያት መሄድ የተሻለ አይደለም ይላሉ? ክርስቲያን መስዋእትነትን እንደ ክርስቶስ “ይህ ጽዋ ከእኔ አይለፍ” ብሎ መፀለይ የለበትም ወይ? ሽጉጥ ስለያዝንስ ከሥጋ ሞት እናመልጣለን ማለት ነው ወይ? ዳዊት ጎልያድን በአዲት ትንሽ ጠጠር እንደገደለው መጽሐፍ ቅዱስ አስተምሯል፡፡ የሥናፍጭ ቅንጣት ታህል እምነት ቢኖራችሁ ይህንን ተራራ ተነስተሕ ሂድ ብትሉት ይሄድላችኋል ተብለን የተማርነውስ የት ይውደቅ? በነገራችን ላይ የሥነናፍጭ ቅንጣት ስንል ትንሽ ማለት አይደለም ይልቁንም ምንም እንከን የሌለው፣ ሙሉ እምነት ማለት ነው፡፡ የስናፍጭ ቅንጣት ሙሉ በሙሉ ድቡልቡል ስለሆነ ከዚያ ምሳሌ የተወሰደ ነው፡፡ ሌላው አሁንም መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረን ታሪክ አናኒያ፣አዛርያ እና ሚሳኤል ከእሳት ነበልባል የወጡት በእግዚአብሔር ስላመኑ ነው ወይስ እራሳቸውን ለመከላከል ሽጉጥ ስለያዙ? አሁንም ወደ ሌላ ቃለ ምልልስ እንሂድ ስለ ቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፖለቲከኛ ናቸው ሃሜት ተጠይቀው መማራቸው ፖለቲካ እንዳሰኛቸው ጠቅሰዋል፡፡ እዚህ ላይ ማስረጃ ቢኖረው ጥሩ ነበር፡፡ እንደእኔ ሀሳብ መቼም የሰው ልጅ የማገናዘብ ጥበብ ተለግሶታል እና እንዴት እንግሊዘኛ ተናገሩ ተብለው ፖለቲከኛ ይባላሉ፡፡ አሁንም ወ/ሮ እጅጋየሁን ያንገበገባቸው ነገር ጳጳስ የእንግሊዘኛ አስተርጓሚ ሊያስፈልጋቸው እንደማይገባ እና እንግሊዘኛ ጠንቅቀው ማወቅ እንደሚገባቸው ነው፡፡ ብዙ ማወቁ በጣም ጥሩ ነው ካላወቁም አስተርጓሚ ኖረ አልኖረ በእምነቱ ላይ የሚያመጣው ተጽኖ ምንድነው? ከዚህ ቀጥለው “ጳውሎስን የሚተካ ሰው የለም አሁንም” ብለዋል፡፡ በመጀመሪያ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ብዬ ላስተካክለው እና እርሳቸውን የሚተካ ሰው እንደሌለ እንዴት አወቁ? ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለወይ? እግዚአብሔር በተለያዩ ዘመናት ብዙ ሐዋርያትንና ነገሥታትን “እንዳስነሳ አያዉቁም እንዴ? ቅዱስ ዳዊትን ከእረኝነት አንስቶ አላነገሰውም ወይ? ይህ አባባል እግዚአብሔር ሁሉ ነገር የሚቻለው መሆኑን ጥርጣሬ ውስጥ አያስገባም ይላሉ? እዚሁ ጥያቄ ላይ ሌላው የመለሱት ነገር አቡነ ጳውሎስን የሚተካ እንደማይኖር ሲናገሩ በአሜሪካን ሀገር በሀገር ፍቅር ሬድዮ ላይ ቀርበው አንድ ኤቢሲዲ ያማያውቁ አባት “እንዴ ወ/ሮ እጅጋየሁ ሃምሳ ስንት ጳጳስ ባለንበት የሚተካቸው የለም” ይላሉ እንዳሉዎት ተናግረዋል፡፡ እግዚአብሔር ይቅር ይበልን እንጅ ሌላ ምን ይባላል? ወ/ሮ እጅጋየሁ አንድ አባት ኤቢሲዲ አላወቁም ተብለው መሰደብ (መወቀስ) አለባቸው ? ኤቢሲዲ ማወቅ የአባትነት መለኪያ ያደረገው ማን ነው? አለማወቅስ ሃጢያት ነው ወይ? ሃጢያቱ አለማወቅን አለማወቅ ነው፡፡ እያወራን ያለው ስለ መንፈሳዊ ሕይወት ነው፡፡ የመንፈሳዊ ሕይወት ዓላማው  መንግስተ ሰማያት መግባት ነው፡፡ ታዲያ የመንግስተ ሰማያት መግቢያ  ጥያቄው ኤቢሲዲ ይሆን? ስንት የማናውቃቸው በዱር በገደሉ ተሰደው ይህቺን ዓለም ንቀው የሚኖሩ አሉ እኮ ታዲያ እነርሱ የግድ ኤቢሲዲ ማወቅ አለባቸው ወይ? እነዚህ ኤቢሲዲ የማያውቁ አባት (በእርስዎ አጠራር) ይህንን ሲናገሩ ሁላቸውም በአንድ ሚዛን ቢቀመጡ አቡነ ጳውሎስን እንደማይተኩ እንደነገሯቸው ገልፀውልናል፡፡ ግዴለዎትም ወ/ሮ እጅጋየሁ እዚህ ላይ ገድል ሰርቼአለሁ ብለው አያስቡ ይልቁንም ፈራጅ እኔ ነኝ የምመዝናችሁ እኔ ነኝ እያሉ ነው:: አቡነ ጳውሎስን እንደማይተኩ እንዴት አወቁ? መቼም ነብይ ነዎት እንዳልል ነብይ ኤቢሲዲ የማያውቁ አባት ብሎ አይሳደብም፡፡
      እንቀጥል፡- ብዮንሴ ቤተ ክርስቲያን አረከሰች ብሎ ሕዝቡ ተቃውሞ እንዳሰማ ሲጠየቁ ተዋቂ ሴት እንደሆነች መልሰዋል፡፡ በተጨማሪም በፖለቲካም ይሆን በዘፈን ተዋቂ ተዋቂ ነው ብለዋል፡፡ በመጀመሪያ ማንም በሀጢያት የጎደፈ ሰው ቤተ ክርስቲያን ገባም አልገባም የሚረክሰው እራሱ ነው፡፡ ቤተክርስቲያንን ሊያረክስ አይችልም፡፡ እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ጉዳይ ቢዮንሴ ኃጢያተኛ ናት እያልኩ አይደለም:: ይህንንማ አልልም እኔ ማነኝ እና ሰው የምመዝን “የእራሱ አይበቃ የሰው ጠበቃ” እንደሚባለው፡፡ ግን ጥያቄዬ ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ስለ ተዋቂነት የሚወራበት ነው ወይ? ስለ ጽድቅ ነው የምናወራው በዓለማዊ ተዋቂ የሆነ ሰው ፃድቅ ነው ማለት አንችልም፡፡ ወ/ሮ እጅጋየሁ የሕዝቡ ጥያቄ የሚመስለኝ ከቤተ ክርስቲያን ዶግማና ቀኖና አንፃር አንድ ጳጳስ ሴት ሰላም ማለት ይችላል ወይ የሚለዉ ነዉ? በእርግጥ መልሱን እኔ አላውቀውም ግን ከዶግማና ቀኖና እንፃር ቢመልሱት የተሻለ ይሆን ነበር፡፡ ስለ ተዋቂነት ከማንሳት፡፡ ሌላው ስለ አቡነ ጳውሎስ ደመወዝ ተጠይቀው “እድሜ ለአቡነ ጳውሎስ ጳጳሶችን ከዚያ ከጉሮኖ አውጥተው ምን የመሰለ ቤት እንዲኖሩ አድርገዋል” ብለዋል፡፡ የእኔ ጥያቄ ወ/ሮ እጅጋየሁ አባታችንን ለከንቱ ውዳሴ እያጋለጧቸው አይደለም ወይ በሰዎች ላይ ቢያድርም ሁሉን የሚፈፅም እግዚአብሔር አይደለም ወይ?(ከኃጢያት በስተቀር)፡፡ በቤተ ክህነት ተፈጥሮ ስለነበረው ብጥብጥ ሲጠየቁ ደግሞ በእርሳቸው ላይ (አቡነ ጳውሎስ) ምንም ድርድር የለኝም ብለዋል፡፡ ይህ ድርቅ ያለ መልስ ግን አንድ ጥርጣሬ አጭሮብኛል፡፡ ወ/ሮ እጅጋየሁ ነገሮችን በትህናና በማስረጃ ማስረዳት ሲችሉ ድርቅ ብለው ድርድር የለኝም ማለት ወገንተኛነት (ፖለቲካ) እንጂ እውነት ለቤተ ክርስቲያን መቆርቆር ነዉ?
      አቶ ታምራት ላይኔ አቡነ ማርቆርዮስን አስነስተው አቡነ ጳውሎስን እንደተኩ ለተጠየቁት ጥያቄ እኔ አላውቅም ብለዋል፡፡ ነገር ግን በዚሁ ቃለ ምልልስ ላይ የፓትርያርክ አመራረጥ ፍፁም ሕጋዊ እንደነበርና አቡነ ጳውሎስን ኢህአዴግ እንዳላስቀመጣቸው በእርግጠኝነት ተናግረዋል፡፡ ታዲያ እኔ አላውቅም እና ሕጋዊ ምርጫ ነበር የሚሉት ሐሳቦች እንዴት ይታረቁ? ኢህአዴግ አላስቀመጣቸውም ካሉ አቶ ታምራት ላይኔ ኢህአዴግ አልነበሩም ማለት ነዉ? ስለ ማያውቁት ነገርስ ከመናገር መጠየቅ አይሻልዎትም ነበር ወይ? በመጨረሻ ቃለ ምልልስዎ ላይ መልዕክት ሲያስተላልፉ በሌሎች እምነት ተከታዮች በጋዜጣና በአደባባይ ፀብ እንደማይወጣ ነው፡፡ እኛ ስሌላው ምን አስጨነቀን ባያወጣስ? መጨነቅ ያለብን የእኛ ጸብ በጋዜጣ ለምን ወጣ ሳይሆን ለምን እንጣላለን ለምን በሰላም አንኖርም የሚለው አይደለም ወይ? አሁንም ሲቀጥሉ በግል ጥላቻ እከሌ ታሀድሶ እየተባለ ረብሻ መኖር እንደሌለበት ነው፡፡ ረብሻ መፈጠር እንደሌለበት እኔም አምናለሁ፡፡ እከሌ ተሐድሶ ነው አይደለም ለሚለው ደግሞ ውሳኔውን ለቅዱስ ሲኖዶስ ብንተወው የተሻለ ነዉ:: ባለፈው ቅዱስ ሲኖዶስ ብዙ ግለሰቦችንና ማህበራትን ታሀድሶ ብሎ ለይቷል፡፡ ታዲያ የእርስዎ ሀሳብ እነዚህ ተሀድሶ አይደሉም ነው? መቼም ከቅዱስ ሲኖዶስ እርስዎን አላምን እኔ ምን አደርጋለሁ፡፡
      በመጨረሻም፡- እነዚህ ሐሳቦቼና ጥያቄዎቼ የተወሰኑት ናቸው፡፡ ሙሉ ቃለ ምልልሱ ላይ ብዙ ጥያቄዎች ቢኖሩኝም እነዚህን ቅድሚያ ሰጥቻለሁ፡፡ ወ/ሮ እጅጋየሁ ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ ቢሰጡኝ በጣም ደስ ይለኛል፡፡ እኔም ከአጉል ጥርጣሬ እወጣለሁ፡፡ በቅርቡም መፅሐፍ እንደሚጽፉና ብዙ ጉድ እንደሚያወጡ ነግረውናል፡፡ ነገር ግን መጽሐፉ ግለሰቦችን ከመውቀስ ይልቅ በመጽሐፍ ቅዱስ የተደገፈ ማስረጃ ያለው፣ ለሰው አስተማሪ ቢሆን ይመረጣል ብዬ ሐሳብ እሰጣለሁ፡፡ ነገር ግን እንደዚሁ ቃለ ምልልስ ለአንድ ግለሰብ ጠበቃ ሆኖ መቅረብ መጽሐፉንም እንኳንስ ታላላቅ ሰዎች ቀርተው በአስራዎቹ እድሜ ያሉና ማንበብ የቻሉ ሁሉ ሊቀበሉት አይችሉም፡፡ ሰው ማማት ከአንድ ለቤተ ክርስቲያን ተቆርቋሪ ነኝ ከሚል ሰው አይጠበቅም፡፡ ለሕብረተሰቡም ፋይዳው ያንን ሰው እንዲጠላው ማድረግ ካልሆነ ሌላ ነገር የለም፡፡ ሀሳቤን ስቋጭ የተከበሩ ወ/ሮ እጅጋየሁ ባነሳኋቸው ሐሳቦች ላይ ቅሬታ ካለዎት ይቅርታ ልጠይቅዎት ዝግጁ ነኝ፡፡
                                                               እግዚአብሔር ልቡና ይስጠን

                                                                                               
                                     
                                                                     E-mail  :     esksta@gmail.com

No comments:

Post a Comment