Wednesday, February 13, 2013

አንተ ያላከበርከውን ህዝብ ማን እንዲያከብርልህ ትፈልጋለህ?

Archieves
እንደሚታወቀው  ጋዜጦችና ሌሎች የመገናኛ ብዙሃን ሀሳብ በነፃ የሚንሸረሸርባቸው /የህዝብ አንደበት ናቸው/:: ከዚህም የተነሳ የአንዱ ሀሳብ ለሌላው ትክክል ላይሆን ይችላል:: አረ እንዲያውም ጭንቅላትን ሁሉ የሚያዞሩ ሊኖሩ ይችላሉ:: ነገር ግን ፀሀፊው ሀሳቡን በነፃ የመግለፅ መብት ስላለው የፈለገውን ቢፅፍ መብቱ ነው:: በሌላ በኩል ደግሞ መልስ መስጠትም መብት ነው:: ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ ሪፖረተር ጋዜጣ እሁድ ነሐሴ 27/2004 ዓ.ም እትም ላይ አለማየሁ ሰይፉ የተባለ ወንድማችን የፃፈውን ካነበብኩ በኋላ ነው:: ፅሁፉን እንዳነበብኩ ሀሳብ ልስጥ አልስጥ በሚል ክርክር ውስጥ ነበርኩ:: ነገር ግን ሀሳብ መስጠት እንዳለብኝ ውስጤ እንደ ኤርታሌ እሳተ ጎመራ ፈንቅሎ ወጣ:: ሀሳቤንም ለመስጠት ወሰንኩ:: በእርግጥ በብዙዎቹ የአቶ አለማየሁ ሀሳቦች እስማማለሁ:: ነገር ግን ሀሳብ ለመስጠት የወሰንኩበትና ብዙ ጊዜ ስነገሩ የምሰማቸው ጥቂት የማይዋጡልኝ ሀሳቦች አሉ:: ለአቶ አለማየሁ ጽሁፍ መነሻ የሆነው በቀድሞው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ህልፈት ህዝቡ ያሳየው በጨዋነት የተሞላ ሃዘንና በውጭው አለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስለሚያወሩት ያልተገባ ወሬ ነው:: በመረጃ ያልተረጋገጠ ወሬ የሚያወሩ ሰዎችን እኔም እንደ አቶ አለማየሁ እቃወማለሁ:: በኢትዮጵያውን ወጣቶች ደምም ስልጣን የሚሹ እንዳለ አቶ አለማየሁ ገልጸዋል:: ይህ እውነት ሀሳባቸው ከሆነ ሲያምራቸው ይቅር ነው የኔ ሃሳብ:: ሊሆን እንደማይችልም ጠንቅቀው ሊያውቁ ይገባል:: እኔ ያልተስማማሁበትና አቶ አለማየሁ በፅሁፉ መግቢያ ላይ ያነሳው ነጥብ በአወዛጋቢው የ97 ምርጫ ወቅት የቅንጅት አመራሮችን “ህዝቡ በትክክል ተረድቶ አይደለም የመረጣቸው” እያሉ አንዳንድ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ይናገሩት የነበረውን ሃሳብ ማስተጋባቱ ነው:: የእኔ ሙሉ እምነት ደግሞ “ህዝብ ምን ጊዜም ትክክል ነው፣ አይሳሳትም” ነው:: ይህን ነገር ለማጠናከር አንድ አባባል ልጥቀስ::  “በእብድ ሃገር እብዱ ማነው ቢሉት ጤነኛው ሰው ነው” አለ የላል የሃገሬ ሰው:: ይህ የሚያስረዳን ምንድነው ብለን ብንጠይቅ እንደሚታወቀው አንድ ሰው እብድ /የአእምሮ በሽተኛ/ የምንለው ከሌላው ሰው የተለየ ነገር ስለሚፈጽም ነው:: አይበለውና በአንድ ከተማ ውስጥ ያሉ ሁሉም ሰዎች እብድ /የአእምሮ በሽተኛ/ ቢሆኑና አንድ ሰው ብቻ ሙሉ ጤነኛ ቢሆን እብዱ የሚሆነው ጤነኛው ነው:: ምክንያቱም ከሌሎች ሁሉ የተለየ ነገር የሚፈጽመው እሱ ስለሆነ ነው:: ይህን ወደ አቶ አለማየሁ ሀሳብ ስናመጣው ወደድንም ጠላንም ህዝብ ከወሰነው ጥሩም ይሁን መጥፎ ትክክል ነው:: ከህዝብ ውሳኔ በላይ ምን አለና? ጥቂቶች ስላልተስማማን ብቻ የህዝብ ውሳኔ ትክክል አይደለም የምንልበት ምንም ምክንያት የለም:: ትክክል ያልሆነው እራሳችን ነው:: ህዝቡ ተሳሳተ በሚለው ሀሳብ የምንስማማ ከሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ በስህተት የተሞላ ነው:: ይህ ደግሞ በፍፁም ሊሆን አይችልም:: አቶ አለማየሁ አሁነም እደግመዋለሁ “በእብድ ሃገር እብዱ ማነው ቢሉት ጤነኛው ሰው ነው” የሚለውን ከግምት ብናስገባው የህዝብ ውሳኔ ከሆነ ስህተትም ቢሆን ትክክል ነው ብዬ አምናለሁ:: ደግሞስ ህዝቡን እናንተ ተሳስታችኋል እኛ ነን የምናውቅላችሁ የሚልና ውሳኔውን የማያከብር አካል /ፓርቲ/ ካለ የመድበለ ፓርቲ አስፈላገነት ምን ላይ ነው? ህዝብስ ምን በወጣው ለውሳኔ ይወጣል:: መቼም እንደ ህግ ባለሙያነትህ ስለመድብለ ፓርቲ ከእኔ ይልቅ አንተ ጠንቅቀህ ታውቃለህ:: ህዝብን የተለያየ አማራጭ ማሳየት የፖርቲዎች ስራ ነው:: ህዝቡም መሰለኝ ያለውን የመምረጥ መብት አለው:: ውሳኔው ትክክል ነው አይደለም ማለት የፖርቲዎች ስራ አይደለም:: ሌላው አቶ አለማየሁ ያነሳው ነገር በውጭ ያሉት ፅንፈኞች ህዝቡ ለምን ሀዘን ወጣ የሚል ቅራኔ እንዳላቸው ነው:: እነዚህ አካላት በጣም ስህተት ናቸው:: ህዝቡ የፈለገውን የማድረግ መብት አለው:: በእነርሱ ጭንቅላትም ህዝቡ ማሰብ የለበትም:: እዚህ ላይ ግን የማነሳው ጥያቄ አቶ አለማየሁ በውጭ የሚኖሩ ፅንፈኞች ህዝብን ለምን ሀዘን ወጣ ማለት እንደማይችሉ ተስማምተናል:: ምክንያቱን የህዝብ ውሳኔ መሻር ስለማይችል እነዚህ አካላት ህዝቡ በስህተት ነው ሀዘን የወጣው ባይ ናቸው:: አቶ አለማየሁ አንተም ህዝቡ በትክክል ሳይረዳ ነው የመረጣቸው /የቅንጅትን አመራሮች/ የሚለውን ሀሳብ አስተጋብተሃል:: እንደ እኔ እንደእኔ ህዝቡ ሀዘን መውጣቱ ስህተት ነው ማለት እና ህዝቡ በስህተት ነው የመረጣቸው ማለት ልዩነቱ ምን ላይ እንደሆነ ለአንተ ጥያቄ ላቅርብልህ:: ለዚህ ነው ሌሎች ህዝብን እንዲያከብሩ ስትፈልግ አንተ በቅድሚያ ማክበር አለብህ የሚል ሀሳብ በርእሴ የጠቀስኩልህ::

በመጨረሻም ስለ ኢሳት ቴሌቭዥን ያነሳኀው አንድ ነጥብ አለ:: ኢሳት ያልጨበጠ ወሬ እንደሚያቀብል ገልጸህልናል:: ግን ሁሉም የኢሳት ወሬዎች ስህተት ናቸው ወይ? ስለ ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ህመም የአገር ውስጥ ሚዲያዎች ቄሱም ዝም መጽሀፉም ዝም ባሉበት ጊዜ መጀመሪያ የሰማነው ከኢሳት አይደለም ወይ? ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚፈጸም ነገር የምንሰማው ከአገር ውስጥ ሚዲያዎች ሳይሆን ከቢቢሲ አልጀዚራ ዊኪሊክስ እና የመሳሰሉት የውጭ ሚዲያዎች ነው:: ስለሃገር ውስጥ ሚዲያዎች ቀጣይ እመለስበታለሁ:: የሳምንት ሰው ይበለን::

No comments:

Post a Comment