Saturday, March 9, 2013

የስኬት ቁልፎች(The key to success)

ስኬት አንድ የታቀደ እቅድ(ግብ)በትክክል መፈፀም ማለት ነው፡፡ ከዚህ ዐረፍተ ነገረ መረዳት የምችለው ነገር ቢኖር ከስኬት በፊት ምንጊዜም የታቀደ ግብ ሊኖር እንደሚገባ  ነው፡፡ አንድ እቅድ ያላቀደ ሰው የፈለገው ቢሊዮነር አልያም ደግሞ የስልጣን ባለቤት ቢሆን እርሱ ስኬታማ ሊባል አይችልም:: በተመሳሳይ አንድ ተማሪ ኢንጅነር የመሆን ፍላጎትና አላማ እያለዉ ሳይፈልገዉና በትምህርት ሚንስቴር አስገዳጅነት ህክምና ገብቶ የተዋጣለት ዶክተር ቢሆን እርሱም ስኬታማ አይደለም::ምክንያቱም ስኬቱ ሊለካ የሚችለው ያቀደውን ግብ ከማሳካትና  እና አለማሳካት ጋር ነው፡፡ አንድ ለረጅም አመታት ለመግዛት ያቀደ ፓርቲ በጉልበትም ይሁን በዲሞክራሲያዊ መንገድ ያን ያቀደውን ያህል አመት ከገዛ ብቻ ነው ስኬታማ ሊባል የሚችው፡፡ ምናልባት ይህን እቅዱን ለማስካት የሚወስዳቸው እርምጃዎች ለህዝቡ ጎጂ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም ለህዝቡ የተሻለ ፓርቲ ቢመጣና ስልጣኑን ካቀደው አመት በፊት  ቢለቅ ለህዝቡ ጠቃሚ ሲሆን ስልጣን የለቀቀው ፓርቲ ግን ስኬታማ አይደለም፡፡ ይህ የፓርቲዎች ግብና የህዝብ ፍላጎት አለመጣጣም ነዉ ብዙዉን ጊዜ መሪዎች (በተለይም የአፍሪካ ) ምርጫ በመጣ ቁጥር የሚሸበሩት ስለሆነም አንድ ሰው/ድርጅት ግብ ሲያስቀምጥ ሌላውን የማይጎዳ መሆን ይገባዋል፡፡ ስኬት ግብ ለሚያቀምጡ ብቻ የተሠጠች ነች ማለት ነው፡፡ ለዚህም ነው “ If you fail to plan, you are planning to fail’ የሚሉት ምሁራን፡፡ከስኬት ቁልፎች መካከል አንዱ ግብ ማስቀመጥ(Goal setting) ሲሆን ሌሎች ደግሞ የዉስጥ መነሳሳት(Motivation) እና ጽናት (persistence) ናቸዉ::

       1.  ግብ ማስቀመጥ ( Goal setting)

ማንኛውም ስኬታማ መሆን የሚፈልግ ሰው እቅድ ማቀድ እንዳለበት ከተስማማን እቅዱስ ምን ምን ማሟላት አለባቸው? የሚለውን ጥያቄ ማንሳቱ ጠቃሚ ነዉ፡፡  ማንኛውም ዓይነት እቅድ “SMART ” መሆን አለበት:: ትርጓሜውም እንደሚከተለው ይተነተናል፡፡
S- Specific ( ግልጽና የተወሠነ)
M-Measurable (የሚለካ)
A- Achievable (ሊሳካ የሚችል)
R- Realistic (እውን ሊሆነ የሚችል)
T- Time framed ( በጊዜ የተወሰነ)

i)      specific ( ግልጽና የተወሠነ)

እቅድ (ግብ) በግልፅ የሚታወቅ መሆን ይገባዋል፡፡ ግልጽነት የሚጎድለዉ እቅድ እንዴት እንደምናሳካዉ ለማወቅ ከባድ ነዉ::ብዙ ሰዎች ግባቸውን ሲጠየቁ የተሻለየምትለዋን ቃል በማስቀደም ሌሎችን ፍላጎታቸውን ያስከትላሉ፡፡ የተሻለ ትምህርት፣ የተሻለ ቤት፣ የተሻለ ገቢ ፣የተሻለ የስልጣን ቦታ ወዘተ ይላሉ፡፡ ይህ አይነቱ ግብ ግልጽነትና ዉሱንነት ይጎድለዋል፡፡ ለስኬታማነትም ሊያበቃን አይችልም፡፡ እንደነዚህ አይነት ሰዎች ብዙ ጊዜያቸው የሚያጠፉት ከአንዱ አንዱ በመንከራተትና በመወዛገብ ነው፡ የተረጋጋ ህይወት ለእነርሱ ተረት ነው፡፡ የተሻለ ገቢ ለማግኜት የሚያቅድ ሰውና የ3000 ብር ደመወዘኛ የ3200 ብር ደመወዝ ያለው የስራ ማስታወቂያ ከወጣ ያለ ጥርጥር ስራውን ይቀይራል፡፡ ምክንያቱም እቅዱ የተሻለ ማግኜት ነውና፡፡ ለዚህም ነው እንዳንድ ሰዎች ከእድሜያቸው በላይ መስሪያ ቤት ሲቀያይሩ የሚኖሩት፡፡ በተመሳሳይ የተሻለ ትምህርት የሚፈልግና ዲግሪ ያለዉ ሰው በአጋጣሚ መንገድ ጠፍቶበት በዩኒቨርሲቲ በር ሲያለፍ የድህረ-ምረቃ ትምህርት ማስታወቂያ ቢያነብ ትምህርቱ ይጥቀመውም አይጥቀመውም ዘሎ ገብቶ ይመዘገባል፡፡ ተምሮ ሲወጣ ግን በህይወቱ ምንም ዋጋ ላይጨምር ይችላል፡፡ በአጠቃላይ ግብ በግልጽ ተወስኖ የተቀመጠ መሆን ይገባዋል፡፡ የተሻለ ገቢ በማለት ፈንታ በወር ማግኜት የሚፈልገውን የገንዘብ መጠን ቢያቀምጥ ይመረጣል፡፡ የተሻለ ትምህርት በማለት ፈንታም ዲግሪ፣ ማስተርስወይም ፒ.ኤች. ዲ እና የመሣሰሉትን ቢያቀምጥ ይመረጣል፡፡

ii). Measurable (የሚለካ)

ሌላው ግብ ስናስቅምጥ ማስተዋል የሚገባን ነገር ግባችን የሚለካ መሆን አለበት፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰዎችን የሚረዳ ድርጂት ለማቋቋም ያቀደ ሰው ምን ያህል ሰዎችን እንደሚረዳ በግልፅ ማስቀመጥ አለበት፡፡ ቤት ለመሰራት ያቀደም ሰው ቢሆን የቤቱን ስፋት አይነት እና የመሳሰሉትን በግልፅ  ማስቀመጥ አለበት፡፡ አለበለዚያ አንድ ሰው ብቻ የምታሰገባ ቤት ቢሰራም ቤት ቤት ነውና እቅዱን እዳሳሣካ ሊቆጥረው ይችላል፡፡ በመሆኑም ማንኛውም ግብ የሚያስቀምጥ ሰው ግቡ የሚለካ መሆን አለበት፡፡

iii)      Achievable (ሊሳካ የሚችል)

አሁንም ግብ ስናስቀምጥ ግባችን ሊሳካ የሚል መሆኑን ማረጋገጥ አለብን፡፡ ይህን በምሳሌ ለማስረዳትም አንድ የ7ኛ ክፍል ተማሪ ዛሬ ላይ ሆኖ የዛሬ 10 ዓመት ፒ.ኤች.ዲ ዲግሪዉን እንደሚይዝ ቢያቅድ እቅዱ ሊሳካ የሚችል አይደለም፡፡ ምክንያቱም ስርዓተ-ትምህርቱ ከ7ኛ ክፍል ወደ ፒ.ኤች.ዲ. ዲግሪ በ10 ዓመት ያጠናቅቅ ዘንድ አይፈቅድለትም፡፡ በኢትዮጵያ ስርዓተ ትምህርት መሠረት ከ7ኛ ክፍል ፒ.ኤች.ዲ. ዲግሪ  ለመያዝ ቢያንስ 14 ዓመታትን ይፈጃል፡፡ ስለሆነም ይህን እቅድ ያቀደ ሠው እቅዱን ሊያሳካ አይችልም፡፡ ስለዚህም ሁጊዜ ግብ ስናስቀምጥ ሊሳካ የሚችል መሆኑንና አለመሆኑን ማሠብ ይኖርብናል፡፡

iv)      Realistic  (እውን ሊሆን የሚችል)

አራተኛው ግብ ሊያካትተው የሚባው መስፈርት ደግሞ እውን ሊሆን የሚችል መሆኑን ነው፡፡ ይህ ቀጥታ ከተፈጥሮ ጋር የሚያያዝና ልንቀይራቸው የማንችላቸውን ነገሮች ማቀድ እንደሌለብን የሚያስገነዝብ ነው፡፡ “change the changeable, accept the unchangeable” 
እንዲሉ ምሁራን በተፈጥሮ እውን ሊሆን የማይችልን ነገር ማቀድ ድካሙ ነው ትርፉ፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው “የዛሬ ዓመት መልዓክ ለመሆን ቢያቅድ እቅዱ እቅድ መሆኑ ቀርቶ ቅዠት ነው የሚሆነው፡፡ ስለሆነም ግባችን በገሃዱ አለም እውን ሊሆን የሚች መሆን አለበት፡ 

v)     Time framed ( በጊዜ የተወሰነ)

 የመጨረሻውና ግብ ስናስቀምጥ ማካተት ያለብን ነገር ግባችን በጊዜ-የተወሰነ መሆኑን ማረጋገጥ ነው፡፡ ይህ ችግር ከሌሎች ማሟላት ከሚገቡን ነገሮች የበለጠ ጎልቶ የሚታይ ነው፡፡ “መኪና ሳልገዛማ አልሞትም” ሲል የምንሠማው ሰው መኪና መቼ እንደሚገዛ ግን አያውቀውም፡፡ የዛሬ 20 አመትም ይህንን ሲደግመው እናሠማለን፡፡ ግብ ስናስቀምጥ ምን ጊዜም በጊዜ የተወሰነ መሆን ይኖርበታል፡፡ አለበለዚያ ነገ እሠረዋለሁ እያልን እድሜያችንን መፍጀታችን ነዉ፡፡
በአጠቃላይ ለስኬት አንዱ ቁልፍ ግብ ማስቀመጥ ሲሆን ግብ ስናስቀምጥም እነዚህን 5 ነገሮች ማካተት አለበት፡፡ ግባችን እነዚህን ነገሮች ሲያሟላ እያንዳንዱ እንቅስቃሴያችን ግባችንን ከማሳካት ጋር ይሆናል፡፡
እነዚህ ማንኛውም ግብ ሊያሟላቸው የሚገቡ ነገሮች ቢሆኑም የበለጠ ስኬታማ ለመሆን ተጨማሪ በግብ ውስጥ መካተት እንዳለባቸውም የተለያዩ ምሁራን ይናገራሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የተወሠኑትን ለመጥቀስ ያህል ግብ በምናስቀምጥት ጊዜ ግባችን ሰፊ መሆን አለበት፡፡ ግባችን በጣም ትንሽ  ከሆነች በቁርጠኝነት እንድንሠራ እያደረገንም፡፡ የ200 ብር የገቢ ጭማሪ ብናቅድ ይህን እንዳሣካን ባለንበት ቀጥ ብለን ነው የምንቀረው፡፡ ስለዚህ ግባችን ሠፊ መሆን አለበት:: ሌላው ግባችን ማካተት ያለበት ነገር ደግሞ ዉጣ ውረድ የሚጠይቅ መሆኑን ማረጋገጥ አለብን፡፡ ስኬት የዉጣ ውረድ ውጤት ነው፡፡ ነገሮች አልጋ በአልጋ ከሆኑልን ብዙም ውጤታማ አንሆንም፡፡ የተወሳሰቡ ሰራዎችን የሚከተል ግብም ተመራጭ ነው፡፡ ሁሌ ተመሳሳይ የሆነ ነገር ስንሠራ ብዙዎቻችን እንሰለቻለን፡፡ በመሆኑም የበለጠ ስኬታማ ለመሆን ግባችን ውስብስብ ስራዎች የሚፈልግ መሆን አለበት፡፡ 

     ሰዎች ለምን ግብ አያስቀምጡም? 

ስኬታማ መሆንን የማይፈልግ ሰው ይኖራል ብሎ ማሠቡ ተገቢ ባይሆንም ግብ የማናስቀምጥ ግን ብዙዎቻችን ነን፡፡ ከስኬት ቁልፎች አንዱ ግብ ማስቀመጥ እደሆነም ከላይ ለማየት ሞክረናል፡፡ ነገር ግን ግብ ሳያስቀምጡ ስኬት ላም አለኝ በሰማይነው፡፡ ታዲያ ሰዎች ለምን ግብ አያስቀምጡም? ብለን መጠየቅ ያሥፈልገናል፡፡
ግብ ላለማስቀመጥ ዋናው ምክንያት የምንፈልገውን አለማወቅ ነው:: ማንኛውም ሰው የሚፈልገውን ማወቅ ቀላል መስሎ ሊታየው ይችላል፡፡ ነገር ግን የምንፈልገውን በትክክል ማወቅ እጅግ አስቸጋሪ ነገር ነዉ::ምክንያቱም ፍላጎታችን በየጊዜዉ የሚቀያየር በመሆኑ ነዉ::ለዚህም  ነው ያየነው ሁሉ የሚያምረን፡፡ የሚያዝናና ኳስ ስናይ እግር ኳስ ተጨዋች መሆን ያምረናል፣ የኦሊምፒክ ሰሞን ደግሞ ሯጭ መሆን ያምረናል፡፡ ፊልም ስናይ አርቲስት መሆን እንፈልጋለን፣ አንድ የፈጠራ ስራ ስናይ ጥሩ ኢንጂነር መሆን ያምረናል፣ የሲ አይ.ኤ ንና ሞሳድን ዝና ስንሰማ ሰላይ መሆን ይከጅለናል ::የተሳካ ቀዶ ጥገና ስንሰማ ደግሞ ዶክተር መሆን በእጅጉ እንመኛለን:: አሪፍ ህንፃ ስናይ ባለ ሐብት መሆን እንቋምጣለን፡፡ ኧረ ስንቱ…፡፡ ስለዚህ  የእኛ ትክክለኛ ፍላጎት የትኛው ነው? ፍላጎታችንን በትክክል ካወቅን ግብ ማስቀመጥ አይከብደንም፡፡ “ነገር በምሳሌ ጠጅ በብርሌ” እንዲሉ አንድ ወጣት የስኬታማነትን ቁልፍ ለማወቅ ፈልጎ ዝነኛውን የግሪኩ ፈላስፋ ሶቅራጥስን የስኬትን ቁልፍ እንዲነግረው ጠየቀዉ ይባላል፡፡ ሶቅራጥስም ወጣቱን ና እየሄድን እነግርሃለሁ ብሎ በባህር ውስጥ እየተራመዱ መሄድ ጀመሩ ፡፡ እየሄዱ እያለም ሶቅራጥስ ወጣቱን ምን እንደሚፈልግ ዳድም ይጠይቀዋል፡፡ ወጣቱም የስኬት ምስጢርን እንድትነግረኝ ፈልጌ ነው ይለዋል፡፡ ባሕሩ መሀል እንደደረሱ ሶቅራጥስ ወጣቱን አንገቱን ይዞ አሰጠመው፡፡ ወጣቱም አየር ለማግኘት ይፈራገጥ ጀመር፡፡ ሶቅራጥስ ግን ሊለቀው አልቻለም፡፡ ወጣቱም ኧረ እባክህ ልቀቀኝ ልትገለኝ ነው እያለ ቢጮህም ሶቅራጥስ አለቀቀውም፡፡ ከጥቂት ደቂቃ በኋላ ሶቅራጥስ ወጣቱን ከውሃው አወጣውና ለምን ይፈራገጥ እንደነበርና እንዲለቀው የጠቀበትን ምክንያት ይጠይቀዋል፡፡ ወጣቱም አየር ፈልጌ ነዉ ይለዋል፡፡ሶቅራጥስም ወጣቱን “አየህ አየር እንደሚያስፈልግሀ ስታውቅ እንደዚህ ከተፈረገጥክ ስኬታማ መሆን ከፈለግህም መጀመሪያ ምን እንደምትፈልግ እወቅ” ብሎ መለሰለት ይባላል፡፡ ስለዚህም ወደ እንቅስቃሴና ትጋት የምንገባው ውስጣችን እንድናገኘዉ የሚፈልገዉን ነገር ማወቅ ስንችል ነው፡፡ ማንኛውም ስኬታማ መሆን የሚፈልግ ሰው በመጀመሪያ ፍላጐቱን ማወቅ ግድ ይለዋል፡፡ ነገሩን ስናጠቃልለው ሰዎች ግብ የማያስቀምጡበት ዋነኛው ምክንያት ፍላጐታቸውን ማወቅ አለመቻላቸው ነው፡፡ ግብ ከማስከመጣችን በፊት ፍላጐታችንን ጠንቅቀን ማወቅ ታላቅ የቤትሥራ ይሆናል፡፡

  2. የውስጥ መነሳሳት (Motivation) 

ግብ ስላስቀመጥን ብቻ ስኬታማ እንሆናለን ማለት አይደለም፡፡ ግባችንን ለማሳካት ያላሰለሰ ጥረት ያስፈልገናል፡፡ በመሆኑም ሁለተኛው የስኬት ቁልፍ ውስጣዊ መነሳሳትን መፍጠር ነው፡፡ ይህን ውስጣዊ መነሳሳታችንን ለማምጣት ደግሞ ያቀድነውን እቅድ በተለያዩና ሊታዩን በሚችሉ ቦታዎች ማስቀመጥ  ይመከራል፡፡ ያስቀመጥነው ግብ ሁልጊዜ ስናየው የበለጠ ለመስራት እንነሳሳለን፡፡ ሌላው ውስጣችንን ለማነሳሳት ልንጠቀምበት የምንችለው ነገር ግባችንን ካሳካን በኋላ ልናገኘው የምንችለውን ስሜት በማሰብ ነው፡፡ ግቤን ሳሳከ ምን አያለሁ፣ምን እሰማለሁ፣ ምንአይነት ስሜት ይሰማኛል የሚሉትን ጥያቄዎች ሁል ጊዜ በማንሳት ውስጣዊ መነሳሳትን ልናመጣ እንችላለን፡፡ 

3     3 .  ፅናት (persistence)

   ስኬት ጽናት ለሌላቸዉ ጀርበዋን የምትሰጥ ወይዘሮ ናት፡ከእያንዳንዱ ስኬታማ ሰዉ በስተጀርባ ጽናት ይኖራል፡፡ነገሮች ሁሉ አልጋ በአልጋ ሆነዉለት ስኬታማ የሆነ ማግኜት ይከብዳል፡፡  በምሳሌ ለማስረዳት ያህልም ሁለት ዋሽንት የሚነፉ ሰዎች ነበሩ ይባላል፡፡አንደኛዉ ሲነፋ ሁሌም ዝናብ ይዘንባል ፡፡ሌላኛዉ ሲነፋ ግን አይዘንብም፡፡ዋሽንት ሲነፋ ዝናብ በሚዘንብለት ሰዉ የሚያዩት ሁሉ ይገረሙበታል፡፡ ሁለቱም ግን ተመልካች አላቸዉ፡፡ከእለታት በአንድ ቀን ዋሽንት ሲነፋ ዝናብ የማይዘንብለትን የሚመለከቱት ሰዎች ሲነፋ የሚዘንብለትን የሚመለከቱትን ሰዎች ዋሽንት ሊያሰሙዋቸዉ ጋበዙዋቸዉ፡፡ተጋባዦችም ዋሽንቱን ከሰሙ በሁዋላ ለጋበዙዋቸዉ ሰዎች እነርሱም በተራቸዉ ዋሽንት ሲነፋ ዝናብ የሚዘንብለትን ሰዉ ያዩት ዘንድ ጋበዙዋቸዉ:: ተጋባዦች ሲያዩ ሰዉዬዉ ሲነፋ ከቆየ በሁዋላ ዝናብ ይዘንብ ጀመር::  በጣም ተገረሙ ::ዋሽንት የሚነፋዉንም ሰዉየ እርሱ ሲነፋ ለምን ዝናብ እንደሚዘንብ ይነግራቸዉ ዘንድ ጠየቁት::ሰዉዬዉም "አይ እኔ ስነፋ አይደለም ዝናብ የሚዘንበዉ ነገር ግን ዝናብ እስከሚዘንብ ነዉ የምነፋዉ"ብሎ መለሰላቸዉ ይባላል::አዎ እኛም ያቀድነዉ እስከሚዘንብልን ድረስ መጽናት ያስፈልገናል:: ይህ ካልሆነ ግን ስኬትን ማምጣት ከባድ ነዉ::በመጨረሻም 
      "CHANGE YOUR WAY BUT NOT YOUR GOAL" ብዬ ላብቃ
              መልካም የስኬት ጊዜ!!!

No comments:

Post a Comment