Friday, February 22, 2013

እግዚዞ! እንዲህም ተጀምረ?



ረቡዕ የካቲት 13 ቀን 2005 ዓ.ም ከቀኑ 9፡00 ሰዓት አካባቢ ለአንድ ቀጠሮ ሜክሲኮ ተገኝቻለሁ፡፡ ከታክሲ እንደወረድኩም የቀጠርኩትን ሰው ስደውልለት ገና መርካቶ እንደሆነ ነገረኝ፡፡ ፀሐዩዋ በጣም ታቃጥላለች፡፡ የአዲስ አበባ ሙቀት ከወትሮዉ በጣም የተለዬ ሆኖዋል፡፡ ጓደኛዬ እስከሚርስ ቦንዙር ከሚባል ካፌ ገብቼ አረፍ ለማለት አሠብኩ፡፡ ወደ ካፌው እያመራሁ እያለ በዕለቱ ከሚታተሙ ጋዜጦቸ መካከል ‘ሰንደቅ’ ጋዜጣ በፊት ገፁ አንድ በጣም አስገረሚ ርዕስ ይዞ ወጥቷል፡፡ “አቡነ ሳሙኤል ቀጣዩ ፓትርያርክ ለመሆን የምረጡኝ ዘመቻ ጀመሩ” የሚል፡፡ ጋዜጣውን ገዝቼ ወደ ካፌው ገባሁና አረፍ ብዬ ጋዜጣዉን ማንበብ ጀመርኩ፡፡ ጋዜጣው ላይ እንዳነበብኩት ከሆነም አቡነ ሳሙኤል የምርጫ ቅስቀሳውን በተጠናከረ ሁኔታ እያካሔዱት ነው ማለት ይቻላል፡፡ እንዴት እንደዚህ ሊሆን ይችላል? እግዚኦ እንጅ ሌላ ምን ይባላል፡፡ በእርግጥ ጽሁፉ 100% ትክክል ነው ማለት ይከብዳል፡፡ ቆይቶም ማስተባበያ ሊወጣበት ይችላል፡፡ ፀሐፊውም ቢሆን ከመሬት ተነስቶ እንደዚህ አይነት ጠንካራ ነገር ይፅፋል ማለትም ይከብዳል፡፡ የሆነው ሆኖ ፅሁፉን እንዳነበብኩት በተለያዩ ድህረ-ገፆች  ላይ አቡነ ሳሙኤል ቀጣዩ የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ሆነው እንዲመረጡ በድብቅ(በህቡዕ) ጫና የሚያደርግ አካል እንዳለ ያነበብኩት ትዝ አለኝ፡፡ እንዲያዉም በአንድ የማህበራዊ ድህረ ገጽ አቡነ ሳሙኤልን ጨምሮ የአምስቱንም እጩ ተመራጮች ስም ዝርዝርና አሁን ያሉበትን ስልጣን አንብቢያለሁ፡፡ሆኖም ሁሉም በማህራዊ ድህረ ገፅ የተለቀቀው ሁሉ እውነት ነው ብሎ መቀበል ስለሚከብድ ከምርጫው በኋላ የሚመጣውን ውጤት መጠበቅ ግድ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ የምርጫ ቅስቀሳ እያካሔዱ መሆኑን ሳነብ ይህ በማህበራዊ ድህረ ገፆች ያነበብኩት ፅሁፍ ውሃ የሚያነሳ መስሎ ታዬኝ፡፡
በእርግጥም እኒህ ሰው ይህን ተግባር ፈፅመው ከሆነ ህዝበ-ክርስቲያኑ በጣም እንደሚያሳዝኑ ጥርጥር የለውም፡፡ ክርስትና ራስን ዝቅ የሚያደርጉበት እንጂ እኔ ስለምሻል ምረጡኝ የሚባልበት እምነት አይደለም፡፡ እንኳንስ በጳጳስ ደረጃ ያሉ ቀርቶ ገና ክርስትናን መማር የጀመሩ ሁሉ ይህን ነገር ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ታዲያ እኒህ በጳጳስ ደረጃ ያሉ ሰው ምረጡኝ ብለው ዘመቻ መጀመራቸው ምን ፈልገው ነው? የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም፡፡ ይህ የምረጡኝ ዘመቻቸውን ሳነብ በእርግጠኛነት እንደማይመረጡ አውቅሁ፡፡ ይህን ስል ጠነቋይ ሆኜ አይደለም፡፡ ይልቁንም አንድ ክርስቲያን እኔ እበልጣለሁ ከሌላው የተሻልኩ ነኝ ካለ ተቀባይነት እንደማያገኝ ስለማውቅ ነው፡፡ ሆኖም ግን ግምቴ ፉርሽ ሆኖ ከተመረጡ በህረተሠቡ ዘንድ ድብቅልቅ ያለ ስሜት መፈጠሩ የማይቀር ነው፡፡ እነዚህ በህብረተሠቡ ዘንድ ጥያቄ ሊያስነሡ ይችላሉ ብዬ የምገምታቸውን ነጥቦች ለመጥቀስ እሞክራለሁ፡፡
የአቡነ ሳሙኤል መመረጥና አለመመረጥ ከጥቂት ቀናት በኋላ የሚታወቅ ቢሆንም አሁን በምንሠማው ነገር የተለያዩ መላምቶች አሉኝ፡፡
የመጀመሪያው መላምቴ እርሳቸው ከተመረጡ በህዝበ ክርስቲያኑ ተቀባይነት የማይኖራቸው እርሳቸው ብቻ ሳይሆኑ ድሮም በተወሠኑ ሰዎች በጥርጣሬ አይን የሚታዉ አስመራጭ ኮሚቴውም ጭምር ነው፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለዉም እንደ አንድ ክርስቲያን ሳስበው መራጩ አካል ምረጡኝ ብሎ የሚዘምትን ጳጳስ ሊመርጥ አይችልም የሚል ግምት በህብረተሰቡ ዘንድ መስረጹ አይቀርም፡፡ የምረጡኝ ዘመቻ ጀምረዋል የሚባሉት አቡነ ሳሙኤልም የአለማዊነት ዝባሌን እያሳዩ ይገኛሉ፡፡ ምናልባትም በዚህ ከቀጠሉ የምርጫ ምልክታቸዉን ማሳወቃቸዉ አይቀርም፡፡ታዲህ በእምነታቸው ጠንካራ የሆኑት መራጮች እነዚህን አባት ይመርጣሉ ተብሎ አይታሠብም፡፡ ነገር ግን የምርጫው ውጤት አቡነ ሳሙኤልን ለፓትርያርክነት የሚያበቃ ከሆነ ህዝብ-ክርስቲያኑ በመረጩ አካልና በአስመራጭ ኮሚቴው ያለውን እምነት ዜሮ እንደሚያስገባው እያጠራጥርም፡፡ አልያም ደግሞ በተለያዩ ድህረ ገፆች እንደሚፃፈው አቡነ ሳሙኤል ፓትርያርክ አድርጎ ለመሾም በህቡዕ ይንቀሳቀሳል የሚባለው አካል ስለመኖሩ የሚወራውን ወሬ እውነትነቱን መቀበሉ ግድ ይሆናል፡፡  በቀላል አገላለፅ ህብረተሠቡ ምርጫው ተጭበርብሯል ወደ ሚለው  ማመዘኑ ሳይታለም የተፈታ ይሆናል፡፡ ባጠቃላይ ምዕመኑ በቤተ-ክርስቲያኒቱ አስተዳዳሪዎች ላይ ያላቸውን እምነት እንደሚቀንሱ እያጠራጥርም፡፡ ይህ ደግሞ በጣም አሳፋሪ እና ቤተ ክርስቲያንቱ የቆመችለትን አላማ እንደረሳች ይቆጠራል፡፡ሌላኛው የምዕመኑ ስጋት ሊሆን የሚችው ነገር ደግሞ በትክክለኛ አቡነ ሳሙኤል ቢመረጡም እንኳን ቤተ-ክርቲያኒቱን እርሳቸው በደንብ ሊመሯት አይችሉም የሚል ይሆናል፡፡ በፅሁፍ እንዳነበብነው ከሆነ በምረጡኝ ዘመቻቸው ብዙ ገንዘብ እንዳፈሠሱና ወደፊትም የውጭ እድል  እንደሚፈቅዱላቸው ቃል የገቡላቸዉ ሰዎች እንደሚኖሩ ነው፡፡ ለስልጣን ይህን ያህል የሚጉዋጉ ከሆነ ስልጣን ከያዙ በኋላም ለቤተ-ክርስቲያኗ ሳይሆን ዉለታ ለመመለስ ብዙ ወጭ ማፍሰሳቸዉ እንደማይቀር መጠርጠሩ ተገቢ ነዉ፡፡በዚህም ምክንያት ምእመኑን ለመንግስተ ሰማያት የማዘጋጀት ተልእኮ ያላት ቤተ ክርስቲያን ስራዋ ሁሉ አለማዊ አጀንዳን ማራገቢያ ሊትሆን የማትችልበት ምንም ምክንያት አይኖርም፡፡ ቤተ-ስርቲያኒቱ ውስጥም ሙስና እንደፈለገ ሲፈነጭበት ማየት እንደማይቀር መገመት ቀላል ነዉ፡፡
እንደ እኔ መላምት ጥያቄ ሊያስነሳ የሚለችው የአቡነ ሳሙኤል መመረጥ ብቻ ላይሆን ይችላል፡፡ አለመመረጣቸውም በተወሠኑ ዘንድ ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም፡፡
ከተለያዩ ድህረ ገፆች እንደሚገለጸዉ አቡነ ሳሙኤል በምርጫ ዙሪያ ከመነሳታቸው በፊት ይህ እርሳቸውን ሊያስመርጥ በህቡዕ ይንቀሳቀሳል የተባለው አካል በመጀመሪያ ሊያስመርጥ ነው ተብሎ የተወራው እርሳቸውን ሳይሆን ሌላ በእራኤል አገር የሚገኙ አባትን እንደሆነ ነበር፡፡
እኒህ በእስራኤል ሃገር የሚገኙ አባት ከተመረጡም ጥያቄው በተመሳሳይ ይነሳል፡፡ ጥያቄ የሚያስነሳውም ሰሞኑን አቡነ ሳሙኤል የምርጫ ዘመቻ የመጀመራቸውን ወሬ ያስነሳው ድብቅ አካል እንደሚኖር ነው፡፡ ህብረተሠቡ ካነበበውና ከሠማው ተነስቶ በእራኤል የሚገኙትን አባት መሾምና አለመሾም የሚጠባበቅ ከሆነ ይህ የአቡነ ሳሙኤልን ጉዳይ ይዞ የተነሳ ድብቅ አካል የህብረተሠቡን አቴንሽን ከእስራኤሉ አባት ወደ አቡነ ሳሙኤል እንዳዞረዉ መጠርጠሩ አይቀርም፡፡ ስለዚህ በድንገት የእስራኤሉ አባትም ከተሾሙ ምእመኑ በአስመራጭ ኮሚቴዉና በመራጮች የሚኖረዉ እምነት ዝቅተኛ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡
ሌላኛው መላምቴ ደግሞ ይህ የአቡነ ሳሙኤልን የምረጡኝ ዘመቻ መጀመራቸዉን መረጃ የሰጠዉ ሰዉ(አካል) ሆን ብሎ አቡነ ሳሙኤል እንዳይመረጡ የሚፈልግ ሊሆንም ይችላል፡፡ይህን ተግባር የሚፈጽመዉ አካል(ሰዉ) በጭፍን ጥላቻ አልያም ደግሞ አቡነ ሳሙኤል ለቤተ ክርስቲያን ስለማይመጥኑ መመረጥ የለባቸዉም የሚል አቁዋም ሊኖረዉ ይችላል፡፡ይህ አቁዋሙ ፍሬ እንዲያፈራ ደግሞ የአቡነ ሳሙኤልን ተቀባይነት ባገኘዉ ሁሉ አጋጣሚ ማሳጣት ይኖርበታል፡፡ከነዚህ ዘዴዎች ዉስጥ ይህ የምረጡኝ ዘመቻቸዉን የሚናገር መረጃ ለህብረተሰቡ ማድረስ አንዱ ሊሆን ይችላል ብሎ መገመቱ ተገቢ ነዉ፡፡እኒህ አባት ከጥቂት አመታት በፊት ከቀድሞዉ ፓትርያርክ አቡነ ዉሎስ ጋር እርስ በርሳቸዉ ሲወጋገዙ እንደነበር ይታወቃል፡፡ምናልባትም በወቅቱ የነበሩት የህትመት ዉጤቶች ያስነብቡት እንደነበረዉ ከሆነ አቡነ ሳሙኤል ቅዳሴ በኢንተርኔት ቢሆን ችግር የለዉም የሚል እምነት እንዳላቸዉ አቡነ ዉሎስ ሲያወግዙ በተቃራኒዉ ደግሞ አቡነ ዉሎስ ታቦተ ጽዮንን አሜሪካ ለጉብኝት ሊልኩዋቸዉ ነዉ ሲሉ አቡነ ሳሙኤል አቡነ ዉሎስን ያወግዙዋቸዉ እንደነበር ሲገለጽ ነበር፡፡ይህን ያስታወሰ ሰዉ አቡነ ሳሙኤል እንዲመረጡ ላይፈልግ ስለሚችል ይህን የአሁኑን የምርጫ ቅስቀሳ መረጃ ሊያስተላልፍ ይችላል፡፡በመሆኑም አቡነ ሳሙኤል የምረጡኝ ዘመቻ ላያካሂዱም ይችላሉ ብሎ ማሰብ ተገቢ ነዉ፡፡እዉነት የምረጡኝ ዘመቻ አካሂደዉ ከሆነ ግን በጣም የሚያሳዝንና ከክርስትና ስርዓት ዉጭ የሆነ ተግባር እንደፈጸሙ ይሰመኛል፡፡ለመላምቶቻችን ፍንጭ  ከጥቂት ቀናት በሁዋላ እንደምናገኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
           እሺ ማንን እንመን?
አቡነ ሳሙኤል የምረጡኝ ዘመቻ ጀምረዋል መባላቸዉ ለጽሁፌ መነሻ ቢሆነኝም በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ግራ መጋባት ከጀመርኩ ሰነባብቻለሁ፡፡በተለይም ደግሞ በዉጭ ሀገር የሚገኙ አባቶችና የሀገር ዉስጥ አባቶች እርስ በርሳቸዉ ሲወጋገዙ ስሰማ በጣም ነዉ የማዝነዉ፡፡ይህን ጽሁፍ እየጻፍኩ እያለ እንኩዋ የሀገር ዉስጥ ሲኖዶስ ለጋዜጠኞች የሰጠዉን ጋዜጣዊ መግለጫና በዉጭ ሀገር ያለዉ ሲኖዶስ ተወካይ ለአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ የሰጠዉን ምላሽ በሸገር በኩል እየሰማሁ ነበር፡፡በሀገር ዉስጥ ያለዉ ሲኖዶስ አቡነ ማርቆርዮስ ስላመማቸዉና በራሳቸዉ ፈቃድ ስለለቀቁ እንጅ በእርሳቸዉ ላይ ሌላ ጳጳስ እንዳልተሾመባቸዉ ለጋዜጠኞች ሲገልጹ በአንፃሩ ደግሞ በአሜሪካ የሚገኙት አባቶች አቡነ ማርቆርዮስን የቀድሞዉ ጠቅላይ ሚንስትር ታምራት ላይኔ እንዳባረራቸዉና በላያቸዉ ላይ ሌላ ጳጳስ እንደተሾመባቸዉ ማስረጃም እንዳላቸዉ እየተናገሩ ነበር፡፡ከዚሁ ጋር አያይዘዉም ለሰላም ድርድሩ አለመሳካት የሀገር ዉስጥ አባቶችን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡ይህንም ሲያጠናክሩ የሀገር ዉስጥ ተወካዮች ለሀገር ዉጭ አባቶች የመኖሪያ ፍቃድ እንደሚያሰጡዋቸዉ እንጅ አቡነ ማርቆርዮስ ወደ ቀደመዉ ስልጣናቸዉ እንዲመለሱ ፍላጎት እንደሌላቸዉ አክለዋል፡፡ታዲያ በዚህ መሀል ማንን እንመን? እዚህ ያሉት እኛ ነን ትክክል ዉጭ ያሉትም እና ነን ትክክል ይላሉ፡፡ከሁለቱም ጎን እኛ ነን ትክክል ቢሉም እዉነቱ ግን አንዱ ብቻ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ታዲያ ስህተት የሆነዉ አካል ስህተቱን አለማመኑ ምን ማለት ነዉ? ይቅር መባባል እየተረሳ ነዉ ማለት ይቻላል፡፡በምእመኑ ዘንድ ተቀባይነትም የሚያገኙት ይቅርታን በሚያስቀድሙ ላይ ነበር፡፡ እንዳስተማሩንም ይቅርታ የሚጠይቅ የበደለ ብቻ ሳይሆን የተበደለም ነዉ፡፡ምን ያደርጋል ቲዎሪ ብቻ ሆኖ ቀረ እንጅ፡፡ክርክራቸዉ ሁሉ አንዱ አንዱን የማዉገዝ ዘመቻ ብቻ ሆኖብኛል፡፡ይህ ደግሞ የሁለቱን ዉዝግብ ፖለቲካ እያስመሰለዉ ይገኛል ፡፡እንዲያዉም እንደሰማሁት ከሆነ ኢ.ቴ.ቪ በዉጭ ሀገር በሚገኙ አባቶች ላይ ዶክመንታሪ ፊልም እየሰራ ነዉ፡፡ይህ ደግሞ የለየለት ፖለቲካ ነዉ፡፡ እዉነቱ የት እንዳለ እነርሱ የሚያዉቁት ቢሆንም ህብረተሰቡ ግራ በመጋባትና በአባቶች ላይ ጥርጣሬ ማሳደሩ የማይቀር መሆኑ ያሳዝናል፡፡ እዉነት ለመናገር የሌላዉን ባላዉቅም እኔ በቤተ ክርስቲያን አባቶች ላይ ያለኝ እምነት እየቀነሰ ነዉ ሁሉንም አባቶች ባይሆንም፡፡
 እግዚአብሔር ለሀይማኖት ሙዋች አባት ይስጠን!!!  

Friday, February 15, 2013

የጎጃም አርሶ አደሮችን የቅጣት ዉርስ (ሌጋሲ)ማን ይፋቀዉ?

የአባት እዳ ለልጅ ይባል ነበር ድሮ
    ባያት እዳ ገባሁ እኔማ ዘንድሮ
የግጥሙን ወርቅ ለጊዜዉ እንተወዉና ሰሙን ብቻ ይዘን እንቀጥል::
እንደ መነሻ:በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ አንድ ትምህርት አለ::በመጽሃፍ ቅዱስ  ኦሪት ዘፍጥረት(Genesis) ላይ እንደተጻፈዉና የቤተ ክርስቲያን አበዉ ሊቃዉንት እንዳስተማሩን እግዚአብሔር አምላክ አዳምን ከፈጠረዉ በሁዋላ በኤደን ገነት አኖረዉ:: የህይወትንም ዛፍ እንዲበላ ፈቀደለት::ሰዉ ብቻዉን ይኖር ዘንድ መልካም አይደለምና የህይወት አጋር የምትሆነዉን ከግራ የጎን አጥንቱ ወስዶ ሄዋንን(የህያዋን እናት) ፈጠረለት::አዳምና ሄዋን በገነት እየኖሩ ሳለ እግዚአብሔር አንድ ትዕዛዝ ሰጥቶዋቸዉ ነበር::ይህም ክፉዉንና ደጉን የሚያሳዉቀዉን እጸ በለስን እንዳይበሉ ነበር::በእባብ አሳሳችነት ሄዋን እንዳይበሉ የታዘዙትን እጽ በላች ለአዳምም ሰጠችዉ::እነሆ እግዚአብሔርም አዳምን ከገነት አስወጣዉ እንዳይበሉ የታዘዙትን ዕጽ በልተዋልና::ጥሮ ግሮ እንዲበላም  እግዚአብሔር ፈረደበት::የአዳም ሀጢያትም ለልጅ ልጁ ሁሉ ይተላለፍ ነበር::ነገር ግን እግዚአብሔር አዳም ከገነት ተባሮ ይቀር ዘንድ አልወደደም::ለአዳምም ቃል ገባለት::”ከልጅ ልጅህ ተወልጀ ነፃ አወጣሀለሁአለዉ::ቃል የገባለትንም ፈፀመለት::ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ አዳምን ከሃጢያቱ አዳነዉ::አዳም ነፃ ወጣ::ለልጅ ልጅ ይተላለፍ የነበረዉም የሀጢያት ዉርስ (ጥንተ አብሶ) ተደመሰሰ::”እግዚአብሄር የአዳምን የእዳ ደብዳቤ ቀደደለትተብሎ እንደተፃፈዉ::
እግዚአብሔር አዳምን ከልጅ ልጁ ተወልዶ ባያድነዉ ኖሮ የአዳም የልጅ ልጆች ባልሰሩት ጥፋት(ዕፀ በለስን ሳይበሉ) ሀጢያተኛ ይባሉ ነበር::መልካም እየሰሩ ቢኖሩም መጨረሻቸዉ መንግስተ ሰማያት ሳይሆንገሃነበ እሳትይሆን ነበር::አሁን ግን እግዚአብሔር አድኑዋቸዋል::ይህ ቃል ኪዳን ከተፈጸመ ከ2000 ዓመታት በላይ ሆኖታል::አሁን ባለንበት ዘመን ኢህአዴግ ሀገሪቱዋን መምራት ከጀመረ ወዲህ በጎጃም አርሶ አደሮች ላይ እየተካሄደ ያለዉን ከአያት ወደ አባት ከዚያም ወደ ልጅና የልጅልጅ እያለ የሚቀጥለዉን አድሎአዊ የመሬት ክፍፍልና ዉርስ ሳይ ይህን 2000 ዓመታት በፊት የተፈጸመ ታሪክ እንዳስታዉስ አድርጎኛል::ታሪክ እንደሚነግረን በፊዉዳሉ  ዘመን ስርዓቱን ከተቃወሙት ክፍሎች መካከል የጎጃምና ባሌ አርሶ አደሮች ይገኙበታል:: አሁንም በጎጃም አርሶ አደሮች ላይ እየተደረገ ያለዉ አድሎአዊ የመሬት ክፍፍል አርሶ አደሮችን ለአመጽ የሚቀሰቅስ ነዉ::የዚህ አድሎአዊ አሰራር ገፈታ ቀማሽ የሆኑት አርሶ አደሮች በደርግ ጊዜ ስልጣን ነበራችሁ የሚባሉ ወገኖች ናቸዉ::እነዚህ ወገኖች በደርግ ጊዜ ያላግባብ መሬት ይዛችሁ ቆይታችሁዋል በሚል ሰበብ አሁን እንዲተዳደሩበት እጃቸዉ ላይ የቀረዉ ከሌላም ማህበረሰብ እጅግ ያነሰ ነዉ::በአንጻሩ ደግሞ የአሁኑ መንግስት ሹማምንት በራሳቸዉ ስም ይቅርና ገና በ5 አመት ልጃቸዉ ስም መሬት አላቸዉ:: መንግስታችንን 40 ዓመት ይንገሱ ብለን ከተዉን ደግሞ  መቼም ሼም የሚባል አልፈጠረባቸዉምና ገና በተረገዙ ልጆች ስምም መሬት ሊቀራመቱ ይችላሉ:: ይህ ሁኔታም የሚያመለክተዉ ብአዴን/ኢህአዴግ የሚመራዉ መንግስት በእነዚህ ወገኖቻችን ላይ የበቀል ጅራፉን እያሳረፈባቸዉ መሆኑን ነዉ::ምናልባትም እንደተባለዉ እነዚህ ወገኖች በደርግ ጊዜ ስልጣናቸዉን ተጠቅመዉ ከሌላዉ ማህበረሰብ የበለጠ መሬት ይዘዉ ከተገኙ ትርፉን መሬት ብቻ መንጠቅ እየተቻለ ገና ለገና በደርግ ጊዜ ስልጣን ነበራችሁና እንደሌላዉ መብላት አትችሉም ማለት ግልጽ የሆነ -ሰብአዊ ድርጊት መሆኑን ነጋሪ አያስፈልገዉም::በዚህም ምክንያት እነዚሀ ቢሮክራሲዎች የሚባሉት የሌላ ሰዉ መሬት በመከራየት ነፍሳቸዉን ለማሳደር ሲንገላቱ ሲታዩ እጅግ በጣም ያሳዝናሉ::ይህን ሁሉ የሚያደርገዉ ደግሞ ክቡር አቶ አያሌዉ ጎበዜ የሚመሩት የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ነዉ::በዝርዝር ባይሆንም ከዚሁ - ሰብአዊ ድርጊት ይቆጠቡ ዘንድ የኛ ፕሬስጋዜጣ ላይ ለአቶ አያሌዉ ጎበዜ የተጻፈ ማመልከቻ አንብቢያለሁ::በየኛ ፕሬሰ ጋዜጣ የተጻፈዉ ነገር ትክክል ስለመሆኑ እኔም ምስክር እሆናለሁ::ይህን ጉዳይ መጠየቅ የጀመርኩት ዛሬ በጽሁፌ አይደለም::ምንም እንኩዋ በተሰጠኝ መልስ ባልደሰትም ከሁለት አመት በፊት አዳማ ከተማ ዉስጥ አንድን የኢህአዴግ ባለስልጣን ጠይቄዉ ነበር::ነገር ግን ጉዳዩ የክልሉ መንግስት እንደሆነ ከመጥቀስ ዉጭ ይህ ነዉ የሚባል አጥጋቢ መልስ አልሰጠኝም ነበር::እንዲያዉነጋዴ ስንቁ ስለተቀማ ሳይሆን የጉዋደኛዉ ስለቀረ ነዉ የሚቆጨዉአይነት አይሁንብኝና ይህ ቢሮክራሲ እያሉ መሬትን ነጥቆ ባዶ እጅን የማስቀረት ተግባር የሚካሄደዉ በአማራ ክልል ጎጃም ዉስጥ መሆኑ ደግሞ በጣም ይገርማል::እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ነገር ጎጃም ላይ የሚደረገዉ የመሬት ንጥቂያ ለምን በሌሎች የሀገራችን ክፍሎች ላይስ አይተገበርም? እያልኩ እንዳልሆነ ነዉ::ይህን የምመኝ ከሆነማ ግልጽ የሆነ ምቀኝነት ይሆንብኛል::”ትዉልድ ይዳን ትምህርት በኛ ይብቃእንዲሉ የአሁን ዘመን ተማሪዎች የስቃይ ስቃይማ እዚያዉ ጎጃም ብቻ ይበቃል::ሆኖም ግን ይህ ተግባር የሚከናወነዉ ጎጃም ላይ ብቻ መሆኑ ጥያቄዎችን በበለጠ እንድናነሳ ያደርገናል::በፊት ይህ ተግባር ጎጃም ላይ እንደሚካሄድ የፌዴራል መንግስት የሚያዉቅ አይመስለኝም ነበር::ሆኖም ግን አዳማ ላይ ስለጉዳዩ ጥያቄ ያነሳሁለት የኢህአዴግ ተወካይ የሌላ ክልል ተወካይ መሆኑና ጉዳዩን እንደሚያዉቅ ሲመልስልኝ በፌዴራል ደረጃም እንደሚታወቅ ተገንዝቢያለሁ::ለክልሉ ህዝብ ቆሚያለሁ የሚለዉ ብአዴንና ለአርሶ አደሩ ጥብቅና እንደሚቆም የሚናገረዉ ኢህአዴግም ራሳቸዉ አርሶ አደሮችን መሬታቸዉን ነጥቆ በራብ አለንጋ ሲቀጣቸዉ ሲታይ እዉነት ይህ ድርጅት ነዉ ህዝብን የሚወክል? ያስብላል::ብአዴን ሆይ በዉኑ የወከሉህ ሰዎች ለልጆቻቸዉ የሚሰጡት አጥተዉ በራብ ሲሰቃዩ ማየት  ያስደስተሃልን!?ብአዴን የተዋጋዉ አንድም አድሎአዊ አሰራርን በመቃወም ነበር::ታድያ እርሱ ጠልቶት ለብዙ አመታት የተዋጋዉን አድሎአዊ አሰራር በሌሎች ላይ ሲተገብረዉ ለምን ሀፍረት እንደማይዘዉ አይገባኝም::ይህ የሚጠቀሙበትን መሬት መቀነስ በአባቶች ብቻ የሚያበቃ አይደለም::ልጆችም ብዙዉን ጊዜ ይህን እጅግ አነስተኛ የሆነ የአባታቸዉን መሬት ይዘዉ ነዉ የሚቀጥሉት::በመግቢያየየአባት እዳ ለልጅ” ያልኩትም ለዚሁ ነዉ::ልጆች ምንም በማያዉቁት ጉዳይ የቅጣቱ ተቁዋዳሽ ይሆናሉ::በዘመነ ኢህአዴግ የተወለዱትን ልጆች አባታቸዉ የደርግ ባለስልጣን ነበር ብሎ መቅጣት ምን ይሉታል? ክቡር አቶ አያሌዉ ጎበዜ ሆይ እስኪ ያስቡት የእርስዎ ልጆች እንኩዋንስ የሚበሉት አጥተዉ ለአንድ ቀን እንኩዋ ያለመኪና በእግራቸዉ ትምህርት ቤት ይሂዱ ቢባሉ የሚሰማዎትን ስሜት::የአቶ አያሌዉ ድርጅት አንድ ቀን ከስልጣል ቢወርድና አይናቸዉ እያየ ጆሮዋቸዉም እየሰማ እርስዎ ሰዉን ቢሮክራሲ እያሉ ሲበድሉ ነበርና ቤትዎንና ያፈሩትን ሀብት ተነጥቆ ልጆቻችሁ ከደጅ ይፍሰሱ ቢባሉ አቶ አያሌዉ ምን አይነት ስሜት እንደሚሰማቸዉ አላዉቅም:: ይህ የበቀል እርምጃ ከአሁኑ የማይቆም ከሆነ የወደፊት የእነ አቶ አያሌዉ ጎበዜ እጣ ፈንታም ከዚሁ የተለየ አይሆንም:: እነርሱ እንደሚሉት ከ40 ዓመት በሁዋላ ቢሆንም ስልጣን መልቀቃቸዉ መቼም አይቀሬ ነዉ::ነገር ግን ይህ አይነት የበቀል እርምጃ ካሁኑ ሊቆም ይገባል::”በራስህ ላይ እንዲደረግ የማትፈልገዉን ነገር በሌሎች ላይ አታድርግይባላልና አሁንም ቢሆን የተከበሩ አቶ አያሌዉ ይህን የሰሩትን የታሪክ ስህተት ሊያስቡበትና ሊያስተካክሉት ይገባል እላለሁ:: ቅሬታ ሰምቶ ጆሮ ዳባ ልበስ ማለት ለኢህአዴግ ብርቅ እንዳልሆነ እናዉቃለን::ታዲያ እነ አቶ አያሌዉ አሁንም ይህን ነገር ችላ ካሉት ሌላ ማን ያስቀረዉ? የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነዉ::ምናልባትም እግዚአብሔር አዳምን ከልጅ ልጁ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ እንዳዳነዉ ሁሉ ከቢሮክራሲዎችም የልጅ ልጅ ተወልዶ አባቶቹን እና አያቶቹን የቅጣት ዉርስ(ሌጋሲ) የሚፍቅ ጀግና የሚነሳበት ሩቅ ላይሆን ይችላል::ይህ ይሆን ዘንድም ምኞቴ ነዉ::የነገ ሀገር ተረካቢ ህጻናት በአባታቸዉ እዳ ሲቀጡ መኖር ሊቆም ይገባል እላለሁ:: ገና በአፍላ እድሜያቸዉ በጭንቅላታቸዉ የሚሰርጽ በቀል እንጅ ሌላ አይደለም::እነዚህ ልጆች ለሀገራቸዉ መልካም ነገርን ያስባሉ ማለት ዘበት ነዉ:: ለሀገራችን ጥሩ የምንመኝላት እርሱዋም ለኛ ጥሩ ስትሆን ነዉ::”ሀገሬ ምን ሰራችልኝ ሳይሆን እኔ ለሀገሬ ምን ሰራሁላትበሉ የሚለዉን ፍልስፍና በበኩሌ አልቀበለዉም::ሀገሬ ጥሩ ነገር ካልሰራችልኝ ምኑ ላይ ነዉ ሀገርነቱዋ?የስቃይ ኑሮማ ሌላ ሀገር ብሄድም ቢያንስ በስደተኛነት ልኖር እችላለሁ:: እናም

   እንደ አንተ ያለ የቸገረ ለት
    አልወለደችም ወይ የጎጃም እናት
ብላ እንዳዜመችዉ አርቲስቱዋ እዉነትም እንዲህ ያለ ግፍ ሲሰራ መፍትሄ የሚፈልግ ወንድ የሚያስፈልግ ይመስለኛል::ይህ አድሎአዊ አሰራር ይቀር ዘንድ ተጎጂዎች ብቻ ሳይሆኑ  ሰብአዊነት የሚሰማዉ ሰዉ ሁሉ መጠየቅ አለበት:: በእርግጥ የአርሶ አደሩ ችግር ይህ ብቻ አይደለም::አንድ ለኢትዮጵያ የሆነዉ ኢ.ቴ.ቪ ሁሌም የአርሶ አደሩን እድገት ቢያቀነቅንም እዉነታዉ ግን ሌላ ነዉ::በተፈጥሮ ጥበቃ አርሶ አደሩ ያለዉ ተነሳሽነት ሁልጊዜ ቢተረትልንም እዉነታዉ ግን አርሶ አደሩ ለተፈጥሮ ጥበቃ ስራ የሚወጣዉ “ብር ትቀጣላችሁ”የሚለዉን የካድሬዎች ማስጠንቀቂያ በመፍራት ነዉ::የአርሶ አደሩ ችግር ተዘርዝሮ የማያልቅ ቢሆንም መንግስታችን የምግብ እንጅ የዲሞክራሲና ነጻነት መብት ጥያቄን መልሰን ችሎቱን ዘግተናል ብሎ ስላወጀብን የምግብ ምንጭ የሆነዉን የአርሶ አደሩን አድሎአዊ የመሬት ክፍፍል ላይ ያለኝን እይታ ጠቅሻለሁ::
 ሰብአዊነት የሚሰማዉ አስተዳደር ይስጠን!!!