Monday, April 8, 2013

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከጀሲካ ምን ይማር ይሆን?


    
 ከሳምንታት በፊት ሀገራችን አንድ ታላቅ እንግዳ አስተናግዳለች::ይህች ታላቅ እንግዳ ጀሲካ ኮክስ ትባላለች::የ32 አመቱዋ አሜሪካዊቱዋ ጀሲካ ኮክስ ሁለት እጆቹዋንም በተፈጥሮ ያጣች ነገር ግን የአዉሮፕላን አብራሪ የሆነች ጀግና ሴት ነች::ይህች ጀግና ሴቶችና አካል ጉዳተኞች እንደሚችሉ አስመስክራለች::ሌሎች በእጃቸዉ የሚሰሩትን ስራ እርሱዋ በእግሮቹዋ አቀላጥፋ እንደምትሰራ ይነገራል::በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለአካል ጉዳተኞች ትምህርት እንደሰጠችም ሰምተናል::የእርሱዋን ታሪክ ስሰማ አዉሮፕላን ማብረር ማንም እንደሚችል ተገንዝቢያለሁ::በአንፃሩ ደግሞ የኢትዮጵያን የአየር መንገድ አብራሪ ለመሆን የሚወስደዉን መስፈርት አስታወስኩ::እጅ የሌለዉ ሰዉ አዉሮፕላን ማብረር ከቻለ የኢትዮጵያን የአየር መንገድ ይህን ሁሉ መስፈርት የሚወስደዉ ለምን ይሆን? የአሁኑን ባላዉቅም ከሁለት አመት በፊት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይወስዳቸዉ የነበሩትን የአብራሪነት መስፈርት በጥቂቱ አዉቃቸዋለሁ::ማንም አብራሪ የመሆን ፍላጎትና ብቃት ስላለዉ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አብራሪ ሊሆን አይችልም ነበር::ይልቁንም ተፈጥሮ የነፈገችዉ መስፈርቶች ለፍላጎቱ መሳካት እንቅፋት  ይሆኑበታል::በዚህም የተነሳ ከህፃንነታቸዉ ጀምረዉ በዉስጣቸዉ ሲቀጣጠል የኖረዉ አዉሮፕላን አብራሪ የመሆን ፍላጎት በዚሁ በተፈጥሮ ምክንያት ህልማቸዉ የተቀጨባቸዉ ሰዎች ጥቂት አይደሉም:: ምንም እንኩዋ አዉሮፕላን አብራሪ የመሆን ብዙም ፍላጎቱ ባይኖረኝም እኔም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚያዎጣቸዉ መስፈርቶች ሰለባ ነበርኩ::መስፈርቱ የሚጀምረዉ  ከቁመት ነበር::1.7 ሜትር ቁመት የማይረዝም ሰዉ ገና በጠዋቱ ከጨዋታ ዉጭ ይደረጋል::ከዚህ በሁዋላ ያለዉን ሂደት በደንብ ባላዉቀዉም ከጉዋደኞቼ እንደምሰማዉ ግን ከቁመት ጣጣ ከታለፈ በሁዋላም እጅግ አሰልችና በጣም ብዙ የጤና ምርመራ(Diagnosis) ማድረግ ይጠበቃል::የልብ የኩላሊት የሳንባ እና የመሳሰሉትን ሁሉ የምርመራ ዉጤት በእድል መወጣት ይገባል::ሌላዉና በጣም የሚገርመዉ ምርመራ ደግሞ በማንኛዉም የሰዉነታችን ክፍል ትንሽም ጠባሳ መገኘት የለበትም:: የልብ የኩላሊት የሳንባ እና ሌሎችም የሰዉነታችን ኦርጋኖች ጤነኛ መሆን እንዳለባቸዉ እኔም ይሰማኛል::በቁመትና ማጠርና  በሰዉነት ላይ ጠባሳ መኖሩ ከዉድድር የሚያስወጣበት ምክንያት ግን እስካሁን ያልተመለሰልኝና የማይዋጥልኝ ሰበብ ነዉ:: በአጋጣሚ እንጨት ቢልጠንና ጠባሳዉ የሚታይ ከሆነ አዉሮፕላን አብራሪ መሆን አንችልም ማለት ነዉ::ሁለት እጅ የሌለዉ ሰዉ አዉሮፕላን አብራሪ መሆን ከቻለ ጠባሳ ያለበት ለምን ማብረር አይችልም እንደሚባል አይገባኝም::
መስፈርቶቹ ህግ አልባ ልማድ(Doctrine) ወይስ ምክንያታዊ?
ህግ አልባ ልማድ(Doctrine) የምንለዉ የህግ መሰረት የለለዉ ነገር ግን በአስፈጻሚዉም ሆነ በህብረተሰቡ ዘንድ በልማድ በህግ እንደተደነገገ መመሪያ የሚቆጠርና ተቀባይነት ያገኘ ልማድ ነዉ::በምሳሌ ለማስረዳትም የሀገራችንን ፍርድ ቤቶች ልማድ ማየት በቂ ነዉ:: የፍርድ ቤት ዳኞች ወደ ችሎቱ ሲገቡ ችሎቱን ሊከታተል የተገኘ ሰዉ ከተቀመጠበት ይነሳ የሚል ህግ የለም::ነገር ግን ማንኛዉም ሰዉ ከተቀመጠበት አለመነሳት እንደወንጀል እየተቆጠረ ይገኛል::በአጋጣሚ ከተቀመጠበት ያልተነሳ ሰዉ ከተገኘም የዳኛዉን ክብር ነክተሃል ተብሎ ወደ ከርቸሌ ይወረወራል::ከተቀመጠበት ያልተነሳ ሰዉ ቢታሰር እንኩዋ  ለምን እታሰራለሁ ብሎ አይጠይቅም ::ምክንያቱም ራሱን እንደወንጀለኛ  ስለሚቆጥር ነዉ::አሳሪዉ አካልም ሰዉየዉ ያለመነሳት መብት እንዳለዉ ስለማያዉቅ እንደወንጀለኛ ያየዋል::ግን ማንኛዉም ሰዉ ዳኛ ሲገባ ያለመነሳት ሙሉ መብት አለዉ::ይህ የህግ መሰረት የሌለዉ ግን እንደ ህግ የሚቆጠር Doctrine ይባላል::
ታዲያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚያወጣቸዉ መስፈርቶች ህግ አልባ ልማድ(Doctrine) ናቸዉ ወይስ ምክንያታዊ?ይህ ጥያቄ ከዚህ በፊትም በዉስጤ ይመላለስ የነበረ ቢሆንም የጀሲካን አብራሪነት ስሰማ  ጥያቄዉ ካለፈዉ በበለጠ አገረሸብኝ::ሁለት እጅ የሌለዉ ሰዉ አዉሮፕላን አብራሪ መሆን ከቻለ በምንም ሂሳብ እጁ ላይ ጠባሳ ያለዉ ሰዉ የአብራሪነት መስፈርትን ላያሙዋላ አይችልም::ስለሆነም በእኔ እምነት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይወስዳቸዉ የነበሩ መስፈርቶች ዶክትሪን ይመስሉኛል::እነዚህ ይወሰዱ የነበሩ መስፈርቶች የአካል ጉዳተኞችን መቻል እዉቅና ካለመስጠት ባሻገር አካል ጉዳተኛ ላልሆኑም ጠንቅ ናቸዉ::
ከአሁን በሁዋላስ?
ሌላኛዉ መነሳት የሚገባዉ ጥያቄ ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከጀሲካ ይማር ይሆን ወይስ “በድሮዉ ጨዋታ” ይቀጥላል? የሚለዉ ነዉ::ጀሲካ ኢትዮጵያ በመጣች ወቅት ዋነኛ የእርሱዋ አስተዋዋቂ የነበረዉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነበር::አየር መንገዱ እርሱዋን ሲያደንቅ ቁመታችሁ አጠረና ጠባሳ ስላለባችሁ አብራሪ መሆን አትችሉም ብሎ ያባረራቸዉ ሰዎች ትዝ አሉኝ::ይህ አየር መንገድ በዚህ ድርጊቱም ሊፀፀትም ይገባዋል እላለሁ:: አንድ ጉዋደኛዬ ስለጀሲካ ሰምቶ”ቆይ አየር መንገድ እኛን ጠባሳ አለባችሁ እያለ ሲያባርር ኖሮ ዛሬ ስለጀሲካ አድናቆት ሲያጎርፍ ሼም የለዉም?”ያለዉ አስቆኛል::ያለፈዉ አልፉዋል:: ለወደፊቱ ግን አየር መንገድ የሚወስዳቸዉን መስፈርቶች ሊመረምራቸዉ እንደሚገባ ይሰማኛል :: ባለንበት በ21ኛዉ ክፍለ ዘመን የድሮን ልማድ(Doctrine) ተቀብሎ መጉዋዝ ሁዋላ ቀርነት ይመስለኛል::አዲስ ድሪምላይነር ሲገዛ ክፉ ልማድንም ጣል ማድረግና ከጀሲካም ትምህርት መዉሰድ ጠቃሚ ነገር ይመስለኛል::ቸር ወሬ ያሰማን!!!
    








No comments:

Post a Comment