ፖለቲካ ነክ የሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮችን
የሚፅፉ ጋዜጠኞችን በፅኑ ማውገዝና ማጣጣል የሰሞኑ ፋሽን ሆኖአል፡፡ በመሆኑም ከቅርብ ቀናት ጀምሮ አንዳንድ ሰዎች በተለያዩ መጽሔቶች ላይ እነዚህ በፖለቲካ ዙሪያ ይጽፋሉ የሚሏቸውን ጋዜጠኞች የማብጠልጠል ዘመቻ ጀምረዋል፡፡ እነዚህ ትችት የጀመሩት ወገኖች ዋናው ጭብጣቸው
ጋዜጠኛ ሆኖ ስለ ፖለቲካ መፃፍ አይቻልም የሚል አንድምታ ያለው ሃሳብ ማስተላለፍ ይመስላል፡፡ በተችዎች አባባልም እነዚህ በፖለቲካ
ዙሪያ የሚፅፉ ጋዜጠኞችን የጋዜጠኛነት ‹‹ሀሁ›› ያልቆተሩ ሲሉ ፈርጀዋቸዋል፡፡ አንዱ ሀሁ ሲል አብሮ ሀሁ፣ ሌጋሲ ሲሉ አብሮ ሴጋሲ
ማለት እየተለመደ መጥቷልና ተቺዎችም ‹‹ሀሁ›› ያልቆጠሩ ሲሉ በፖለቲካ ዙሪያ ይጽፋሉ የሚሉዋቸዉን ጋዜጠኞች ለመወረፍ ይዳዳሉ፡፡
በአንፃሩ ደግሞ እነዚህ ተቺዎች ከዚህ በፊት በጋዜጠኝነት ሙያ ብዙ መስዋዕትነት የከፈሉ እደነበሩ ጠቅሰው ብዙ ጋዜጠኞች ለእስርና ስደት
እንደተዳረጉም ያክላሉ፡፡ ታዲያ እነዚህ ለእስርና ስደት የተዳረጉ ጋዜጠኞች ስለምን ፅፈው ለዚሁ አሠቃቂ ሁኔታ እንደተዳረጉ ለእነዚህ
ሰሞኑን ለተነሱት ተችዎችም ግልጽ ነው፡፡ መቼም ስለ አውሮፓውያን አቀንቃኞችና ኳስ ተጨዋቾች የሚፅፍ ጋዜጠኛ ኢትዮጵያ ደብረው ካልሆነ
በቀር በሌላ ተጽዕኖ ለእስርና ስደት ይዳረጋል ማለት ቀልድ ነው፡፡ ነው ነጋ መሼ ስለኢትዮጵያ መመንደግ የሚያዜም ጋዜጠኛ ይሆን?
ይህማ በጭራሽ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለ ፖለቲካ መፃፍ ሐጢያቱ ምንድነው?
ስለፖለቲካ የሚፅፉ ከሆነ መታሰር ወይም መሰደድ አለባቸው እያሉን ካልሆነ በቀር እነዚህ ተቺዎች፡፡ የጋዜጠኛ ዋናው ተግባሩ ህዝብ
ያላወቀውን ማሳወቅ እና የህዝብን አቤቱታ ለመንግስት ማቀበል ነው፡፡ ማሳወቅ ያለበት ደግሞ ስለ ዘፋኞችና ኳስ ተጨዋቾች ብቻ አይደለም፡፡ ህዝብ በማህበራዊውም፣ በፖለቲካዊውም
በኢኮኖሚያውም ማወቅ ይፈልጋል፡፡ ጋዜጠኛም ይህን ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ መረጃ ለህዝብ ሲያቀብልም እውነታን መሰረት አድርጎ ሙያዊ
ትንታኔ መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ ያየውን እንደወረደ ተናግሮ ብቻ ሊያመጣ የሚችለውን ውጤት ጠንካራና ደካማ ጎኑን ካልተነተነ ምኑ
ላይ ነው ጋዜጠኛነቱ? ያየውን ተናግሮ ዝም ለማለትማ ጋዜጠኝነት መማርም አያስፈልግም፡፡ እንዲያውም ትምህርት መማርም ላያስፈልግ
ይቻላል፡፡ ህፃንም እኮ በተኮላተፈ ቋንቋ ያየውን ይናገራል፡፡ አንድ ጋዜጠኛ በሚፅፈው ፅሁፍ ሊጠየቅ ይችላል፡፡ ይህም የሐሰት ዘገባ
ነው ከተባለ ነዉ፡፡ ስለ ፖለቲካም ይሁን ስለስፖርት እውነቱን አፍረጥርጦ ስለተነተነ ጋዜጠኛ አይደለም ማለት አይንን በጨዉ መታጠብ
ነው፡፡ ብቻ የሚፈለገው እውነተኛ መረጃ ለህዝቡ ማድረስ ነው፡፡ ስለ ፖለቲካ መፃፍ እንቶ ፈንቶ ነው የሚሉት እነዚህ ተቺዎች የአንድ
ሃገር የመኖር ህልውና ፖለቲካ እንደሆነ እነርሱም አያጡትም፡፡ በእነርሱ አባባል ፖለቲካ ‹እንቶፈንሮ› ከሆነ ስለ አውሮፓውያን አቀንቃኞች
መዘገብ ነው ቁምነገሩ? ነዉስ “ቫለንታይን ዴይ” “አፕሪል ዘ ፉል” ምናምን እያሉ ሚዲያን ያህል ነገር በእርባና ቢስ ተረት ጊዜን
ማባከን? ይህን ተቺዎች ይመልሱት :: ማንኛውም ሰው ፖለቲከኛ ነው፡፡ ጋዜጠኛውም፣ መምህሩም፣ ተማሪውም፣ ስራፈቱም፣ ተቺውም ሁሉም
ሰው፡፡ ለእኔ ፖለቲካ ማለት የሐገሬ ጉዳይ እኔንም ያገባኛል ብሎ መገንዘብ ነው፡፡ ሌላ ትርጉም አልሰጠዉም፡፡ የሀገሬ ጉዳይ አያገባኝም
የሚል ሰዉ ካለ እርሱ ደነዝ ነዉ፡፡ የሆነ ጊዜ ነዉ ከ ሁለት ጉዋደኞቼ ጋር ስንጫወት በወሬያችን መሃል የሀገር ጉዳይ ተነሳ
:: አንደኛዉ ጉዋደኛዬ “እኔ ምናገባኝ አንድ እንጀራ አያሳጣኝ እንጂ” ሲል በጣም ታዝቤዉ ነበር::እንዲህ ያለዉ ጉዋደኛዬ ባለዲግሪ
ነዉ:: ደግነቱ ሌላኛዉ ጉዋደኛዬ ደግሞ “12ኛ ክፍል የደረሰ ስለ ሀገሩ አያገባኝም ይላል ወይ” ብሎ ሲወርፈዉ አንጀቴን አርሶት
ነበር:: እነዚህ የሰሞኑ ተችዎች ይህንን እንዳስታዉስ አድርገዉኛል ::ስለሆነም ማንኛዉም ሰዉ የሀገሩ ጉዳይ ሊያሳስበዉ ይገባል
እላለሁ::ደግሞም ብዙዉ ህዝብ የሀገሩ ጉዳይ ያሳስበዋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ ::ከአንዱ አንዱ ልዩነት አለ ብዬ የማስበዉ ደፋርና
ፈሪ መሆን ላይ ነው፡፡ፈሪው ፖለቲከኛ ውስጡ እየተቃጠለ በፍርሀት ቆፈን ተሸብቦ ዝም ሲል ደፋሩ ግን ፊት ለፊት እውነታን ይዞ ይጋፈጣል፡፡
ፖለቲከኛ ለመባል የግድ ፓርቲ መመስረት ላያስፈልግ ይችላል፡፡ ታዲያ እነዚህ ውግዘት እየቀረበባቸው ያሉ ጋዜጠኞች እውነትን አፍረጥርጠው
የሃገሪቱን እውነተኛ ገፅታ ለህዝብ ስላደረሱ ምንድነው ችግሩ? ነው ጋዜጠኛ የሃገሩ ጉዳይ አይመለከተውም? ከኢትዮጵያ ውጭ ሌላ ሃገር
የለንም እያሉ እየተናገሩ ነው፡፡ ስለዚህ እነሱም የሃገራቸው ጉዳይ እደሚመለከታቸው ማመን ግድ ይሆንብናል፡፡ እነዚህ በፖለቲካ ዙሪያ
ይጽፋሉ የሚባለት ጋዜጠኞች የገዥውንም ይሁን የተቃዋሚ ፖርቲዎችን ችግርና የወደፊት ተግዳሮቶች መተንተናቸዉ መመስገን ሲገባቸው ለምን
ስለ ፖለቲካ ይጽፋሉ ብሮ ጉሮ ወሸባ ማለት ጠቀሜታው አይታየኝም፡፡ ወይ በግልጽ እነሱም ስለ አውሮፓውያ አቀንቃኞች መፃፍ አለባቸው
ብሎ መናገር ነው፡፡ እርግጥ ነው አንዱን ተቃውሞ ሌላውን እየደገፉ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት መስራት የአንድ ጋዜጠኛ ስራ አይደለም፡፡
እነዚህ ትችት እየቀረበባቸው ያሉ ጋዜጠኞች ግን እየፃፉ ያሉት ስለ ሃገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ከማንበብ ያገኙትን እውቀት
ነው፡፡ በየድርጅቱም ስላለው ችግር ለህዝብ እያሳወቁ ነው፡፡ በገዥውም ይሁን በተቃዋሚው ሊኖር የሚገባውን ነገር መፃፍ ጥቅሙ እንጅ
ጉዳቱ አይታየኝም፡፡ ፍትህ ይኑር፣ የሃገሪቱ ኢኮኖሚ እያሽቆለቆለ ነው፣ ሰብአዊ መብት ይከበር ብሎ መፃፍ የፅድቅ ስራ ነው፡፡ የግድ
ጋዜጠኛ ስለሆነ ስለ ፍትህ መኖር፣ ስለ ሰብዓዊ መብት መከበረ መፃፍ የለበትም ማለት ጋዜጠኛውን አንደ ሌላ ዜጋና የሀገሩ ጉዳይ
እንደማይመለከተዉ መቁጠር ነው፡፡ ያለዉን ችግር መጠቆም ከምንም በላይ
የሚጠቅመው ህዝቡንና ራሱ ገዥውን ፓርቲ እንጅ ጋዜጠኞችን አይደለም፡፡ አንድ ተችም ጋዜጠኛ ርዕዮተ ዓለምን መተቸት አይችልም ሲል
የተለያዩ ምሁራንን ፅሁፍ ጠቅሶ ለማብረረት ሞክሯል፡፡ ለምን ሺ ምሁር
አይናገርም! ለምንድነው ጋዜጠኛ ርዕዮተ ዓለም የማይተቸው? ህዝቡን ወደ ድህነትና ኢ-ዲሞክራሲያዊነት የሚያጋልጥ ርዕዮተ ዓለም ከሆነ
መተቸት አለበት፡፡ በቃ አካፋን አካፋ ማለት ነዉ ::ጋዜጠኛ የቆመው ለህዝብ ጥቅም እንጅ ለፓሮፓጋንዳ አይደለም፡፡ ችግሩ ርዕዮተ
ዓለሙን መተቸቱ ሳይሆን አንዱን ፓርቲ እየደገፉ የሌላውን እየተቸ የሚፅፉ ከሆነ ነው፡፡ ያለውን ችግር ጠቅሶ የተሻለ ስርዓት ለህዝቡ
ቢመጣ እንደሚሻል አቅጣጫ ማሳየት ከጋዜጠኝነት ስነ ምግባር ጋር የሚያያዝ አይደለም፡፡ ጋዜጠኞች በዩኒቨርሲቲ የሚማሩትን ባለውቅም
ስለፖለቲካ ይፅፋሉ የሚባሉትን ጋዜጠኞች የሚተቹትን ሳይ ግን ‹‹የሃገራችሁ ጉዳይ አያገባችሁም፣ ዝም ብላችሁ ወሬ ማቀበል ነው ስረችሁ››
ተብለው የሚማሩ እመሰለኝ ነው፡፡ ጋዜጠኛ ለህዝቡ የተሻለ ነገር ይመጣ ዘንድ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ ‹‹ከሺ ጦረኛ አንድ ጋዜጠኛ››
ማን ነበር ያለው? ይህን ያለው የሃገርን ነባራዊ ሁኔታ ለህዝብ በማጋለጥ በኩል የጋዜጠኛን ጉልህ ሚና እንጅ ስለ ዘፋኝ የሚተርከዉን ጋዜጠኛ ለመጥቀስ አይደለም፡፡ ‹‹ገዥ
ፓርቲን መልዓክ ተቃዋሚን ሰይጣን›› አድርጎ የሚያቀርብ የሬድዮ ጣቢያና ጋዜጠኛ ባለበት ሐገር ተቀምጠን ድክመትን ለምን አወጣ ተብሎ
የሚተች ጋዜጠኛ ‹‹ሊበሏት ያሰቧትን ወፍ ጅግራ ነሽ ይሏታል›› አይነት ነው:: አንድ ተቺ እነዚህን በፖለቲካ ዙሪያ ይፅፋሉ የምትላቸውን
ጋዜጠኞች ስትሰድብ ‹‹አንዳንድ የነፃው ፕሮስ ሰዎች እነዚህን ጋዜጠኞች ‹‹ድንቁርናን ከየትኛው ት/ቤት ነው የተማሩት?›› ብለዋል
ብላለች፡፡ እህቴ ድንቁርና ማለት የሃገሬ ጉዳይ አያገባኝም ብሎ ቁጭ ማለት ነው:: ከዚህም የባሰ ድንቁርና ደግሞ የሃገራቸዉ ጉዳይ ያገባናል በሚሉት ላይ ዘመቻ መክፈት ነዉ::ስለ አውሮፓውያን አቀንቃኞችና ስፖርተኞች ሌት ከቀን
መዘመር ይሆን እውቀት? ሌላዉ ደግሞ ተቺዋ በጣም ያሳቀችኝ እነዚህ በፖለቲካ ዙሪያ ይጽፋሉ የምትላቸዉን ጋዜጠኞች "ገንዘብ ያሰከራቸዉ "ማለቱዋ ነዉ:: እዉነት ይህ በጣም ያስቃል:: ይህ አባባሉዋ በሁለት አይነት መንገድ ሊተረጎም ይችላል::የመጀመሪያዉ ይህች ተቺ ፖለቲካዊ ነክ ጽሁፎች በህዝብ ዘንድ ተፈላጊና ተነባቢ ስለሆኑ ገንዘብ የበለጠ ያስገኛሉ እያለችን ነዉ:: በህዝብ ተቀባይነት ያገኘ ጽሁፍ ደግሞ ትክክል ነዉ ምክንያቱም ህዝብ ምንጊዜም ትክክል ስለሆነ:: ይልቁንም በገንዘብ የሰከረ ማለት ህዝብ የማይፈልገዉን በግዴታ አንብበዉ ማለት ነዉ:: ሌላኛዉ የተቺዋ አባባል ደግሞ ስለፖለቲካ የሚጽፉ ጋዜጠኞች በተለያየ ተጽእኖ ለእስር ቢዳረጉ ቃሊቲ ብር ይሰጣቸዋል እያለችን ይመስላል:: ይህን እያለች ከሆነ ብዙ ቱጃር ጋዜጠኞች አሉን ማለት ነዉ(ቃሊቲ)::ጋዜጠኛ የብረተሰቡን አንገብጋቢ ነገር ማስቀደም አለበት ምክንያቱም ከህዝብ የበለጠ ነገር የለምና:: ይህ ሲሆን ነዉ ሙያዊ ግዴታዉን ተወጣ የሚባለዉ:: ገንዘብ ለማግኜት ብቻ የቆመ ጋዜጠኛ ማለት የህዝብ ችግር ጉዳዩ ያልሆነና በበላበት ብቻ የሚያጨበጭብ እንጂ መስዋዕት ለመክፈል ዝግጁ የሆነ አይደለም ::ብር ለማግኘት እኮ አሁን እያየን እንዳለዉ በስድስት ሰዓታት ደርሶ አንዱ ሰፈር በሞባይል ቀርጾ ስሙን አሳምሮ ፊልም ብሎ ማሳየትም ይቻላል::ምንም መስዋዕትነትን አይጠይቅም::በነገራችን ላይ ይህች ተቺ ከእነዚህ ጋዜጠኞ ብዙ እውቀት አግኝታ ሊሆን እንደሚችል ተስፋ አደርጋለሁ ፡፡
ማጠቃለያ
የሰው ልጅ በተፈጥሮው መሸነፍን (መበለጥን) አይወድም፡፡
የእነዚህ ተችዎች ዋናው መነሻቸውም ይህ መሰለኝ፡፡ አሸናፊ መሆን ደግሞ በስራ እንጅ በትችት ናዳ እና ስድብ አይደለም:: ጠንክሮ
ሰርቶ ከሁሉም በላይ መሄን ይቻላል፡፡ እንቶ ፈንቶ ይፅፋሉ ብሎ ከመተቸት ይልቅ እንቶ ፈንቶ ምንድነዉ የሚለውን ጥያቄ መመለስ ተገቢ
ነው፡፡ ጋዜጠኛ የሃገሩ ጉዳይ እንደሚመለከተው ጠንቅቆ ማወቅም ይገባቸዋል፡፡ እንቶ ፈንቶ የሚፅፍ የአንባቢን ፍላጎት ሊያረካ አይችልም፡፡
በዚህም ምክንያት ብዙ አንባቢ ያለው ጥሩ ነገር ይፅፋል ማለት ነው፡፡ የሀሳብ ‹ልዕልና› ያለው ምንጊዜም አሸናፊ ነው፡፡ የማን
ጽሁፍ ብዙ አንባቢ እንዳለውና ብዙ እዉቀትን እንደሚያስጨብጥ ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ በእርግጥ የእነዚህ ተቺዎች መምጣት እንዲማይቀር
ቀድሞ ተነግሮን ስለነበር አዲስ አልሆነብንም፡፡ ግን እየሔዱበት ያለው መንገድ በጣም አሳፋሪና ተቀባይነት የሌለዉ እንደሆነ ሊያስቡበት
ይገባል እላለሁ፡፡ በመጨረሻም “እዉነትም ዞምቢዎች እየመጡ ነዉ መሰለኝ”::
No comments:
Post a Comment