Wednesday, October 23, 2013

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ረብሻና መንስኤዉ በዩኒቨርሲቲዉ ምክትል ፕሬዚዳንት እይታ

ካለፉት ጥቂት ቀናት ጀምሮ በደብረ ማርቆሰ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና በአስተዳደሩ መካከል አለመግባባት መፈጠሩ ይታወቃል::አለመግባባቱም አንድ ቀን ረገብ ሌላ ቀን እንደገና ሲያገረሽ እስካሁን ዘላቂ መፍትሄ ሳይሰጠዉ አለ::የፀቡ መንስኤ ከአለባበስና ምግብ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ሲገለፅ መቆየቱ ይታወቃል::ይህ በእንዲህ እንዳለ እሁድ ጥቅምት 10 ቀን 2006 . የአማራ መገናኛ ብዙሃን ከደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር በከተማዋ ልማትና መልካም አስተዳደር ዙሪያ ከከተማዋ ህዝብ ጋር ዉይይት አካሂዶ ነበር::በባህር ዳር ኤፍ ኤም 96.9... የቀጥታ ስርጭት ሽፋን ያገኘዉ ይህ ዉይይት ቀድመን መልሶችን የምናዉቃቸዉ በርካታ ጥያቄዎች ተነስተዋል::ይህን ያልኩበት ዋና ምክንያት ከህዝብ ለሚነሱ ጥያቄዎች ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ድረስ ያሉ አመራሮች የሚሰጡዋቸዉ መልስ ሁሌም ተመሳሳይ በመሆናቸዉ ነዉ::ማንም ሰዉ እነዚህን መልሶች ያዉቃቸዋል::የመልሶቹን ተመሳሳይነት ለተገነዘበ ሰዉ መልስም ከበላይ አመራር ወደታች የሚወርድ ሊመስለዉ ይችላል:: የመጀመሪያዉ አማራጭ አድርገዉ የሚወስዱት ጥያቄዉን ሳይመልሱ ማለፍ ነዉ:: ሌላዉ አማራጭ ደግሞችግሩ መኖሩን አዉቀን ጥናቱን እያጠናቀቅን ነዉ በቅርቡ ችግሩ ይፈታልወይምእንዲህ የተባለዉ ዉሸት ነዉ(የተሳሳተ መረጃ ነዉ)”ይህ ካልሆነ ደግሞይህ ሌላ አጀንዳ ያላቸዉ ሰዎች ወሬ ነዉየሚሉና ከነዚህ ተመሳሳይ መልስ ዉጭ ማግኜት ተመኝቶ መቅረት ነዉ::በዚህ ዉይይት ወቅትም ሁሉም አይነት መልሶች ነበሩ ሲደጋገሙ የዋሉት::ሌላዉን እንተወዉና በዩኒቨርሲቲዉ ዙሪያ የተነሱትን ጥያቄዎችና በዩኒቨርሲቲዉ ምክትል ፕሬዚዳንት የተሰጡትን መልሶች እንያቸዉ::ስለ ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በዋናነት ሁለት ጥያቄዎች ተነስተዋል::የመጀመሪያዉ ጥያቄ የዩኒቨርሲቲዉ የግብርና የትምህርት መስክ(Agriculture campus) ህዝቡ ሳይስማማበት በሀይል ወደ ቡሬ የተወሰደበት አግባብ ሲሆን ሁለተኛዉ ጥያቄ ደግሞ በዩኒቨርሲቲዉ ዉስጥ ስለተከሰተዉ ረብሻ ማብራሪያ እንዲሰጥበት የሚሉ ነበሩ::ለጥያቄዎቹ መልስ የሰጡት የዩኒቨርሲቲዉ ምክትል ፕሬዝዳንት የሰጡዋቸዉ ማብራሪያዎች ከላይ በአማራጭነት ካቀረብኩዋቸዉ የአጠቃላይ የመንግስት አመራር የሚሰጡዋቸዉ መልሶች ሁለቱ ነበሩ::ለመጀመሪያዉ ጥያቄ የሰጡት መልስ ሳይመልሱ ማለፍ ነበር::በነገራችን ላይ የዩኒቨርሲቲዉ የግብርና ትምህርት መስክ ወደ ቡሬ ከመዞሩ በፊት ከህብረተሰቡ ጋር ዉይይት ተደርጎ ባለመስማማት ነዉ ዉይይቱ ያለቀዉ::እንዲያዉም አመራሮቹ ወደ ቡሬ ሊዛወር ነዉ ብለዉ የሚያወሩት የግንቦት 7 ተላላኪዎች ናቸዉ እንጂ ወደ ቡሬ አይሄድም ብለዉ ነበር::አሁን ግን ካምፓሱ ቡሬ ነዉ ያለዉ::
ለሁለተኛዉ ጥያቄም /ፕሬዚዳንቱ የሰጡት መልስ ያዉ እንደተለመደዉ ተማሪዎችን መፈረጅ ነበር:: ምክትል ፕሬዚዳንቱ በመልሳቸዉ መጀመሪያ የተናገሩትን ቆይተዉ ሲያፈርሱ ነበር የዋሉት::ጥያቄዉን መመለስ ሲጀምሩ የፀቡ መንስኤ በአለባበስና ምግብ ምክንያት እንደሆነ ገልፀዋል ::የምግቡ ጥያቄ በፌደራል ደረጃ እንጂ በዩኒቨርሲቲዉ ሊመለስ እንደማይችል ከገለፁ በሁዋላ እንደምሳሌም ከዚህ በፊት 80 ግራም የነበረዉ የስጋ መጠን በዚህ አመት 46 ግራም እንደሆነ አምነዋል::ማብራሪያቸዉን ሲቀጥሉም መጠኑ ቢያንስም በአሁኑ ጊዜ ለተማሪዎች ከሳምንት ሁለት ቀን ስጋ እንደሚቀርብና ማንም ቢሆን ቤቱ ዉስጥ ከሳምንት 2 ቀን ስጋ የሚበላ እንደሌለ በመናገር በሀገራችን አኑዋኑዋር ለመሳለቅ ሞክረዋል::ከአለባበስ ጋር በተያያዘ ስለተከሰተዉ አለመግባባት ሲያብራሩ ደግሞ ከትምህርት ሚንስቴር የወጣዉን መመሪያ በተማሪዎችና በህብረተሰቡ ለማስረፅ ዉይይት እንዳደረጉና ዉይይቱ ፍሬያማ እንዳልነበረላቸዉ ገልጸዋል::ዉይይቱ ባለመግባባት እንደተጠናቀቀና መግባባት ባይኖርም ቀጥታ ተግባራዊ እንደተደረገ ያከሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ መመሪያ ግንዛቤ ለመፍጠር እንጂ ዉሳኔ ለመቀየር ለዉይይት እንደማይቀርብ ተናግረዋል::እዚህ ላይ መላሹ የያዙት አቁዋም ትክክል አይመስለኝም::ምክንያቱም ማንኛዉም ህግ ነክ ነገር ሲወጣ ለህብረተሰቡ ተብሎ ነዉ ::ስለሆነም ህብረተሰቡ ካልተስማማበት ቀጥታ ህጉ ዉድቅ መሆን አለበት ህገ መንግስት ቢሆንም:: ይህ የሚያመለክተዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ የተወሰነ ቡድን ያወጣዉን ህግ ህዝቡ ተቀበለዉም አልተቀበለዉም ተግባራዊ መሆኑ ግድ ነዉ::ያልፈለከዉን ህግ ይጫንብሀል::ለኔ አክራሪነት ማለት ይህ ነዉ ያልተፈለገን የህግ መመሪያ በህዝብ ላይ መጫን::ከዚህ በፊትም ይህን አይነት ነገር በሊዝ አዋጁ ተከስቶ አልፎዋል:: ህዝቡ ሳይወያይበት ቀጥታ ተግባራዊ የሆነዉ የሊዝ አዋጅ ከፍተኛ ተቃዉሞ ገጥሞት እንደነበር ይታወቃል::ይህን ተቃዉሞ የተመለከተዉ መንግስት ህዝቡን ያላወያየነዉ እንዲህ ተቃዉሞ ይገጥመዋል ብለን ስላልገመትን ነዉ በማለት ህጉ ተግባራዊ ከሆነ በሁዋላ ላወያያችሁ የሚል የህፃን ቀልድ መቀለድም ጀምሮ ነበር::ቀድሞ በተወሰነና ተገባራዊ ከመሆን ማንም ሊያግደዉ በማይችል ህግ መወያየትም ጊዜ ከማባከን ዉጭ ጥቅም አልባ ነዉ::ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲም ስህተት ሰርቶዋል ማለት ነዉ እንድ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ማብራሪያ:: በመጨረሻም ምክትል ፕሬዚዳንቱ የራሳቸዉን ትንታኔ ሲያስቀምጡየፀቡ ምክንያት የምግብና አለባበስ አይመስለኝም ይልቁንም ከጀርባዉ ሌላ አጀንዳ ያለዉ ይመስለኛልበማለት ወደ ፍረጃ ሮጠዋል:: ለፍረጃቸዉ ያቀረቡት ማስረጃ ደግሞ ረብሻዉ ማታ ሁለት ሰዓት ላይ በኢሳት ቴሌቪዠን እንደተነገረ ነዉ::ዶክተሩ ግን ስንተኛዉ ክፍለ ዘመን ላይ ነዉ ያሉት ጎበዝ?መረጃ በሴኮንድ ከየትኛዉም አለም በሚደርስበት ዘመን ተቀምጠን የተደረገ ድርጊት መዘገቡ ምኑ ላይ ሌላ አጀንዳ አለዉ የሚያስብል?የሚዲያ ስራ መረጃ ማቅረብ መሆኑንም ረስተዋል::21ኛዉ ክፍለ ዘመን ላይ ያለ ዶክተር እንደዚህ አይነት ትንታኔ ሲሰጥ ከመሳቅ ዉጭ ሌላ ምን ይባላል?ደግሞም ከላይ ራሳቸዉ በአለባበስና በምግብ ምክንያት ፀቡ እንደተነሳ ሲናገሩ ቆይተዉ መጨረሻ ላይ ደግሞ ሌላ ነገር ዘባረቁ::ሳይዘባርቁ መኖር አይቻልም እንዴ አዚህ አገር? በዚህ አጋጣሚ የደብረ ማርቆስን ህዝብም ወቅሰዋል:: ህብረተሰቡ ማተባቸዉን በጥሱ ብለዋቸዉና አስርበዋቸዉ ነዉ እያለ እንደሚያወራ በመጠቆም ይህን ከማለት ይልቅ ህዝቡ ተማሪዎችን ዝም ብሎ መመልከት እንደሌለበትና ከፖሊስ ጎን እንዲቆም ተማፅነዋል:: ዶክተሩ ይህን ቢሉም የከተማዋ ከንቲባ አሳማኝ የሆነ ነገር በመናገሩ ደስ ብሎኛል:: “ተማሪዎች ተበድለዉ ሊሆን ይችላል ግን ህንጻ መሰባበር ተገቢነት የለዉምነበር ያለዉ::ይህ ሁላችንንም ያስማማናል::
በመጨረሻምየሀገራችን አመራሮች ሆይ! እባካችሁ ጭራና ቀንድ ከሌለዉ ፍረጃ ወጥታችሁ ለእዉነት ቁሙ::የእዉነት አመራርና ዶክተርም ሁኑ:: የማይመስል ነገር በመናገር አታስቁን ለማሳቅ እነ ክበበዉ ይበቁናልብየ ልሰናበት

1 comment:

  1. your face is not new for me . i think you are a ginbot 20 highschool & preparatory lumamme civics teacher. is that yours or not? your writng is very nice. berta ketelibet

    ReplyDelete