ከሳምንታት በፊት ሀገራችን አንድ ታላቅ እንግዳ አስተናግዳለች::ይህች ታላቅ
እንግዳ ጀሲካ ኮክስ ትባላለች::የ32 አመቱዋ አሜሪካዊቱዋ ጀሲካ ኮክስ ሁለት እጆቹዋንም በተፈጥሮ ያጣች ነገር ግን የአዉሮፕላን
አብራሪ የሆነች ጀግና ሴት ነች::ይህች ጀግና ሴቶችና አካል ጉዳተኞች እንደሚችሉ አስመስክራለች::ሌሎች በእጃቸዉ የሚሰሩትን ስራ
እርሱዋ በእግሮቹዋ አቀላጥፋ እንደምትሰራ ይነገራል::በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለአካል ጉዳተኞች ትምህርት እንደሰጠችም ሰምተናል::የእርሱዋን
ታሪክ ስሰማ አዉሮፕላን ማብረር ማንም እንደሚችል ተገንዝቢያለሁ::በአንፃሩ ደግሞ የኢትዮጵያን
የአየር መንገድ አብራሪ ለመሆን የሚወስደዉን መስፈርት አስታወስኩ::እጅ የሌለዉ ሰዉ አዉሮፕላን ማብረር ከቻለ የኢትዮጵያን
የአየር መንገድ ይህን ሁሉ መስፈርት የሚወስደዉ ለምን ይሆን? የአሁኑን ባላዉቅም ከሁለት አመት በፊት የኢትዮጵያ
አየር መንገድ ይወስዳቸዉ የነበሩትን የአብራሪነት መስፈርት በጥቂቱ አዉቃቸዋለሁ::ማንም አብራሪ የመሆን ፍላጎትና ብቃት ስላለዉ
በኢትዮጵያ
አየር መንገድ አብራሪ ሊሆን አይችልም ነበር::ይልቁንም ተፈጥሮ የነፈገችዉ መስፈርቶች ለፍላጎቱ መሳካት እንቅፋት ይሆኑበታል::በዚህም የተነሳ ከህፃንነታቸዉ ጀምረዉ በዉስጣቸዉ ሲቀጣጠል
የኖረዉ አዉሮፕላን አብራሪ የመሆን ፍላጎት በዚሁ በተፈጥሮ ምክንያት ህልማቸዉ የተቀጨባቸዉ ሰዎች ጥቂት አይደሉም:: ምንም
እንኩዋ አዉሮፕላን አብራሪ የመሆን ብዙም ፍላጎቱ ባይኖረኝም እኔም የኢትዮጵያ
አየር መንገድ የሚያዎጣቸዉ መስፈርቶች ሰለባ ነበርኩ::መስፈርቱ የሚጀምረዉ
ከቁመት ነበር::1.7 ሜትር ቁመት የማይረዝም ሰዉ ገና በጠዋቱ ከጨዋታ ዉጭ ይደረጋል::ከዚህ በሁዋላ ያለዉን ሂደት
በደንብ ባላዉቀዉም ከጉዋደኞቼ እንደምሰማዉ ግን ከቁመት ጣጣ ከታለፈ በሁዋላም እጅግ አሰልችና በጣም ብዙ የጤና
ምርመራ(Diagnosis) ማድረግ ይጠበቃል::የልብ የኩላሊት የሳንባ እና የመሳሰሉትን ሁሉ የምርመራ ዉጤት በእድል መወጣት
ይገባል::ሌላዉና በጣም የሚገርመዉ ምርመራ ደግሞ በማንኛዉም የሰዉነታችን ክፍል ትንሽም ጠባሳ መገኘት የለበትም:: የልብ
የኩላሊት የሳንባ እና ሌሎችም የሰዉነታችን ኦርጋኖች ጤነኛ መሆን እንዳለባቸዉ እኔም ይሰማኛል::በቁመትና ማጠርና በሰዉነት ላይ ጠባሳ መኖሩ ከዉድድር የሚያስወጣበት ምክንያት ግን
እስካሁን ያልተመለሰልኝና የማይዋጥልኝ ሰበብ ነዉ:: በአጋጣሚ እንጨት ቢልጠንና ጠባሳዉ የሚታይ ከሆነ አዉሮፕላን አብራሪ መሆን
አንችልም ማለት ነዉ::ሁለት እጅ የሌለዉ ሰዉ አዉሮፕላን አብራሪ መሆን ከቻለ ጠባሳ ያለበት ለምን ማብረር አይችልም እንደሚባል
አይገባኝም::
መስፈርቶቹ ህግ አልባ ልማድ(Doctrine)
ወይስ ምክንያታዊ?
ህግ አልባ ልማድ(Doctrine) የምንለዉ የህግ መሰረት የለለዉ ነገር ግን በአስፈጻሚዉም
ሆነ በህብረተሰቡ ዘንድ በልማድ በህግ እንደተደነገገ መመሪያ የሚቆጠርና ተቀባይነት ያገኘ ልማድ ነዉ::በምሳሌ ለማስረዳትም
የሀገራችንን ፍርድ ቤቶች ልማድ ማየት በቂ ነዉ:: የፍርድ ቤት ዳኞች ወደ ችሎቱ ሲገቡ ችሎቱን ሊከታተል የተገኘ ሰዉ
ከተቀመጠበት ይነሳ የሚል ህግ የለም::ነገር ግን ማንኛዉም ሰዉ ከተቀመጠበት አለመነሳት እንደወንጀል እየተቆጠረ
ይገኛል::በአጋጣሚ ከተቀመጠበት ያልተነሳ ሰዉ ከተገኘም የዳኛዉን ክብር ነክተሃል ተብሎ ወደ ከርቸሌ ይወረወራል::ከተቀመጠበት
ያልተነሳ ሰዉ ቢታሰር እንኩዋ ለምን እታሰራለሁ ብሎ አይጠይቅም
::ምክንያቱም ራሱን እንደወንጀለኛ ስለሚቆጥር ነዉ::አሳሪዉ
አካልም ሰዉየዉ ያለመነሳት መብት እንዳለዉ ስለማያዉቅ እንደወንጀለኛ ያየዋል::ግን ማንኛዉም ሰዉ ዳኛ ሲገባ ያለመነሳት ሙሉ
መብት አለዉ::ይህ የህግ መሰረት የሌለዉ ግን እንደ ህግ የሚቆጠር Doctrine ይባላል::
ታዲያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚያወጣቸዉ
መስፈርቶች ህግ አልባ ልማድ(Doctrine) ናቸዉ ወይስ ምክንያታዊ?ይህ ጥያቄ ከዚህ በፊትም በዉስጤ ይመላለስ የነበረ ቢሆንም
የጀሲካን አብራሪነት ስሰማ ጥያቄዉ ካለፈዉ በበለጠ አገረሸብኝ::ሁለት እጅ የሌለዉ ሰዉ አዉሮፕላን አብራሪ
መሆን ከቻለ በምንም ሂሳብ እጁ ላይ ጠባሳ ያለዉ ሰዉ የአብራሪነት መስፈርትን ላያሙዋላ አይችልም::ስለሆነም በእኔ እምነት የኢትዮጵያ
አየር መንገድ ይወስዳቸዉ የነበሩ መስፈርቶች ዶክትሪን ይመስሉኛል::እነዚህ ይወሰዱ የነበሩ መስፈርቶች የአካል ጉዳተኞችን መቻል
እዉቅና ካለመስጠት ባሻገር አካል ጉዳተኛ ላልሆኑም ጠንቅ ናቸዉ::
ከአሁን በሁዋላስ?
ሌላኛዉ መነሳት የሚገባዉ ጥያቄ ደግሞ የኢትዮጵያ አየር
መንገድ ከጀሲካ ይማር ይሆን ወይስ “በድሮዉ ጨዋታ” ይቀጥላል? የሚለዉ ነዉ::ጀሲካ ኢትዮጵያ በመጣች ወቅት ዋነኛ የእርሱዋ አስተዋዋቂ የነበረዉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነበር::አየር መንገዱ እርሱዋን ሲያደንቅ ቁመታችሁ አጠረና ጠባሳ
ስላለባችሁ አብራሪ መሆን አትችሉም ብሎ ያባረራቸዉ ሰዎች ትዝ አሉኝ::ይህ አየር መንገድ በዚህ ድርጊቱም ሊፀፀትም ይገባዋል
እላለሁ:: አንድ ጉዋደኛዬ ስለጀሲካ ሰምቶ”ቆይ አየር መንገድ እኛን ጠባሳ አለባችሁ እያለ ሲያባርር ኖሮ ዛሬ ስለጀሲካ
አድናቆት ሲያጎርፍ ሼም የለዉም?”ያለዉ አስቆኛል::ያለፈዉ አልፉዋል:: ለወደፊቱ ግን አየር መንገድ የሚወስዳቸዉን መስፈርቶች
ሊመረምራቸዉ እንደሚገባ ይሰማኛል :: ባለንበት በ21ኛዉ ክፍለ ዘመን የድሮን ልማድ(Doctrine) ተቀብሎ መጉዋዝ ሁዋላ
ቀርነት ይመስለኛል::አዲስ ድሪምላይነር ሲገዛ ክፉ ልማድንም ጣል ማድረግና ከጀሲካም ትምህርት መዉሰድ ጠቃሚ ነገር
ይመስለኛል::ቸር ወሬ ያሰማን!!!