Sunday, March 17, 2013

ለመሆኑ ትውልዱ ያጣው ምንድነው? ተጠያቂውስ? መፍትሄዉስ?


እርግጥ ነው ይህ ጥያቄ ተገቢ እንዳልሆነ እኔም ይሠማኛል፡፡ ምክንያቱም ትውልዱ ያገኘው ምንድነው? የሚል ቢሆን ኖሮ ጥያቄው የተሻለ ይሆን ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይህን ጥያቄ ላነሣ የወደድኩበት ምክንያት በአንድ የስልጠና መድረክ ሰልጣኞች ይህን ጥያቄ ስለተጠየቁና መልሳቸውን ስሰማ የተሰማኝ ነገር ስላለ ነው፡፡ ጥያቄው በአጠቃላይ በራስን በመግለፅ አመራር (Reflecting leadership) ዙሪያ ሲሆን የህይወት ተሞክሮዎ፣ እቅድዎ፣ ትውልዱ ያጣው እና ተጠያቂው እንዲሁም መፍትሔው ፣አርዓያ የሚያደርጉት ሰዉ? ለምን? የሚሉትን ያካትት ነበር::በጥያቄዎች ዙሪያ ከተሣታፊዎች የተለያዩ ነጥቦች ተነስተዉ የነበረ ቢሆንም እኔ ማንሳት የፈለግሁት ጥያቄ በብዙ ተሳታፊዎች ዘንድ ተመሳሳይ መልስ የተሰጠበትን ሆኖአል፡፡
ከላይ በርዕሴ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ለሠልጣኖች ከተጠየቁት ጥያቄ ውስጥ ትውልዱ ያጣው ምንድነው? ተጠያቂውስ እንዲሁም መፍትሔው የሚል ጥያቄ አንዱ ነበር፡ ለዚህም ከተለያዩ ተሣታፊዎች የተለያዩ ሀሳቦች ተነስተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ድፍረት፣ ወኔ፣ እውቀት፣ ምክንያታዊ መሆን፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ የሐገር ፍቅር፣ ጥሩ መሪ፣ ማንነቱን፣ ሥራ ፣መተሣሠብ፣ ሚዲያ፣ መተማመን፣ እንዲሁም ሁሉን ነገር አጥቷል የሚሉት ትውልዱ ስላጣው ነገር ከተመለሱት ዉስጥ ይገኙበታል፡፡ ለዚህም ነው ትውልዱ ያጣውን ሳይሆን ያገኘውን መጠየቅ ይሻላል ያልኩት፡፡ ትውልዱ ማነቱን አጥቷል ያሉት ተሣታፊዎች ሲያብራሩ ችግሩ የመጣው በግሎባላይዜሽን ምክንያት ትውልዱ የምዕራባዉያንን ባህል እንጂ የኢትዮጵያን እየረሳ እንደመጣ ይናገራሉ፡፡ ለዚህም ተጠያቂው በዋናነት ሚድያው እንደሆነ ያብራራሉ ::በአብዛኛው የኢትዮጵያ ኤፍ ኤም ሬድዮ ጣቢያዎች ስለምዕራባዊያን የጥበብ ሠዎችና እግር ኳስ ጨዋታዎች ሳይደክሙ ሌት ከቀን ማስተላለፋቸው ወጣቱ ትውልድ በአብዛኛው ስለምዕራባዊያን እንጅ ስለሀገሩ እንዳያስብ እንዳደረጉት ይገልፃሉ፡፡ የሃገር ውስጥ ዝግጁቶችም ቢሆኑ ፕሮፓጋንዳ እና ስለፆታዊ ፍቅር እንጅ ትውልዱን ለእውቀት፣ ለለውጥ፣ ለእድገት እዲሁም ለሀገር ፍቅር የሚያነሣሣ ዝግጅት ማቅረብ ጉዳያቸዉ አይደለም ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ በዚህ ሐሳባቸው እኔም አስማማበታለሁ፡፡ አዎ ትውልዱ ማንነቱን አጥቷል፡፡ የፌስቡክ ገጼን ስከፍት አንድ የተመለከትኩት ነገር አለ፡፡ የድሮና የአሁን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ጥያቄ የሚያነፃፅር ፅሁፍ፡፡ የድሮ ተማሪዎች ጥያቄ በአብዛኛው መብትን የማከበር ለምሳሌ መሬት ላራሹ፣ የብሔረ ጭቆና ይቁም፣ ነፃነታችን ይከበርና የመሳሰሉት ነበር፡፡ የአሁን ተማሪ ጥያቄዎች ደግሞ ክሬዚዴይ ይከበር፣ የዴ ኤስ ቲቪ ካርድ ይገዛ፣ የዳቦ ግራም ቀነሠ፣ የቫለንታይን ዴይ ይከበርና የመሳሰሉት ናቸው፡: የምዕራባዉያንን ሰይጣናዊ ፍልስፍና እንደወረደ መቀበል የተለመደ ሆኖዋል፡፡ለምሳሌም እንደምናነበውና እንደምንሠማው ከሆነ የሌዝቢያን ሴቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣትና ግብረ ሰዶማዉያን በሀገራችን እንዲሰበሰቡ መፈቀዱ ማንነትን ማጣት ነው፡: በነገራችን ላይ አንድ ሴትዮ አሉ “ኢየሱስ ያድናል ግብረ ሰዶም ትዉልድን ያጠፋል አምልጡ! “የሚል ጽሁፍ ይዛ አራት ኪሎ አካባቢ የምንትቀሳቀስ::እርሳቸዉን ሴትዮ በግሌ አድንቂያቸዋለሁ:: የምዕራባዊያን ፍላጎት ወደ ሐገራችን ሲዛመት ዝም ብሎ ከመመልከትና መተግበር የበለጠ ማንነትን ማጣት ምን አለ?ይህ ብቻ አይደለም በአዲስ አበባ አንድ አንድ ትምህርት ቤቶች እንግሊዝኛ እንጅ የሃገር ዉስጥ ቋንቋ መናገር ያስቀጣል::እንግሊዝኛ አቀላጥፎ መናገር እዉቀት የሚመስላቸዉም ጥቂት አይደሉም::የዉጭ ቋንቋ መቻል በጣም ጥሩ እና አስፈላጊ ነዉ ::ነገር ግን ይህ ሲሆን የራስን በመርሳትና በመናቅ መሆን የለበትም::ቻይና ዉስጥ ስንት ምሁራን ከቻይንኛ ዉጭ የማይችሉ አሉኮ::ለዚህ ነዉ እኔም ማንነታችንን አጥተናል እያልኩ ያለሁት::ከቋንቋ ጋር በተያያዘ በአንድ ወቅት አንድ የኢህአዴግ ባለስልጣን ሲናገር እንዲህ ብሎ ነበር::”ድሮ ከአማርኛ ዉጭ አትናገሩ ይባል ነበር ::አሁን ደግሞ በአንዳንድ የአዲስ አበባ ት/ቤቶች አማርኛ መናገር ያስቀማል የሚል ማስጠንቀቂያ ጽሁፍ ይለጠፋል::አማርኛ የእጁዋን አገኘች::” ብሎ በቀል የሚመስል መልዕክት ተናግሮ ነበር::ከዚህ ሰዉዬ የተረዳሁት የሀገር ዉስጥ  ቋንቋዎች ቢጠፉም ደንታ እንደሌለዉ ነበር::በመሆኑም ማንነታችንን ያጣን መሪዎቻችንን ጨምሮ ሁላችንም ነን::ከላይ እንደጠቀስኩትም የምዕራባዉያን የፍላጎት ፍልስፍና ዉጤት የሆነዉ ሌዝቢያኒዝም አዲስ አበባችንን እያጥለቀለቃት ከመሆኑ የተነሳ  ሚስቶችችን ወይም ፍቅረኞቻችን ከሌላ የሴት ጓደኛቸዉ ጋር ሲሄዱም መቅናታቸንና መጠርጠራችን አይቀርም፡፡ አቦ በስንቱ እንቅና !
ሌላው በሠልጣኞች የተነሣው ነጥብ ትውልዱ ድፍረትና ወኔ እንዳጣ ነው፡፡ ይህንንም ሲያስረዱ ትውልዱ አንድን የተሣሣተ ነገር ስህተት ነዉ ብሎ ለመናገር በራስ መተማመንና ድፍረት የለውም ይላሉ፡፡ በዚህ ዙሪያ አንድ በመንግስት መስሪያ ቤት የሚሠራ ሰው ሐሳቡን ሲያካፍለን እርሱ ይሠራበት በነበረው መስሪያ ቤት የሚቀርቡት ሪፖርቶች በሙሉ ውሸት እንደሆኑ አስረግጦ ይናገራል፡፡ “እኔም በመስሪያ ቤቱ ለመቆየት ስል የማላምንበትን ውሸት የሆነ ሪፖርት አስተላልፍ ነበር” ሲል ያክላል፡፡ “ይህ ለምን ሆነ ብዬ እንዳልጠይቅ ያባርሩኛል ብየ ስለምፈራ አላደርገዉም ነበር” ሲል ያየዉን እዉነት ተናግሩዋል::ሌሎችም የእርሱን ሐሳብ ሲያጠናክሩ  በእያንዳንዱ የመንግስት መስሪያ ቤት እንደዚህ አይነት ትውልዱን የሚገድሉ ስራዎች ይሠራሉ፡፡ ነገር ግን ያላመንኩበትን አልሠራም የሚል የለም፡፡ ለዚህም ነው ትውልዱ ድፍረትና ወኔ አጥቷል የምንለው ሲሉ አብራርተዋል፡፡ ሐሳባቸውን ሲያጠቃልሉም በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ደስተኛ ሆኖ አይሠራም፡፡ ለመናገር ፈሪ ስለሆነና አማራጭ ስላጣ ነው ይላሉ፡፡ ተሣታፊዎቹ ትውልዱ ሌላም ነገር አጥቷል ይላሉ::መተማመንና አንድነት ከትውልዱ ላይ እንደጠፋ ይናገራሉ:: ዜጎች እርስ በርእሳቸው በጥርጣሬ አይን መተያየት መጀመራቸው ለአንድነታቸውም መላላት ዋናው ምክንያት ነው ይላሉ፡፡ ስለ አንድ ጉዳይ በነፃነት ለመናገር በአካባቢው ያለውን ሰው ማንነት ማወቅን እንደ ቅደመ ሁኔታ ማስቀመጥ የተለመደ እንሆነም ያክላሉ ::እጠቆራለሁ ፣ከስራ እባረራለሁ፣እድገት እከለከላለሁ እና እታሠራለሁ ብሎ መፍራት ብርቅ እንዳልሆነም በአፅንዎት ይናገራሉ፡፡ አሁን አሁን ይላሉ ተሣታዎች  “ሙሰኛን ማጋለለጥ ከስራ መባረርን እደሚያከትል ሁሉም እያወቀዉ ነው፡፡” የድሮው ትውልድ ፍቅር አሁን ላይ ማግኘት እጅግ ከባድ እንደሆነም ይናገራሉ፡፡ ትውዱ እውቀትንም አጥቷል ይላሉ እነዚህ ተሣታፊዎች፡፡ ምንም እንኳ መንግስት ትምህርትን እያስፋፋሁ ነው ቢልም ውስጣቸው ት/ቤት ናቸው ለማለት ይከብዳል ሲሉ ይናገራሉ:: ከተሣታፊዎች ውስጥ ሁለት ያህሉ እንዲያውም እንደ ውድቀት ያነሡት ዩኒቨርሲቲ መመደባቸው እዚያ መማራቸው ነው፡፡ “አዲስ አበባ” ዩኒቨርሲቲ ስሙ እንጂ ውስጡ ባዶ ቀፎ ነው እያሉ ሲያወግዙት ነበር፡፡ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ሊመደቡ በማይፈልጉት የትምህርት መስክ መመደባቸው በእውቀታቸው ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ እንደሆነ ያረዳሉ፡፡
ሚዲያና የሃገር ፍቅርም ትውልዱ ካጣቸው ውስጥ እንዲሚመደቡ በእለቱ ተጠቅሠዋል፡፡ የሀገር ፍቅር በትውዱ ላይ እንዲሌላ ሲያረዱም በአብዛኛው ወጣቱ ኢትዮጵያ ያለው በአካል እንጅ በመንፈስ ሌላ ሃገር በተለይ ምዕራባዊያ ዘንድ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ የሀገር ፍቅር ማለት የባንዲራ ቀለም ያለው ልብስ መልበስ አይደለም:: እንዲሁም ኢትዮጵያ ሐገሬ እወድሻለሁና ኢትዮጵያዊነቴ ኩራቴ ብሎ መዘመር እንዳልሆነም ያክላሉ:: የሀገር ፍቅር ማለት ሐገርን በዴሞክራሲና በኢኮኖሚ አንድትበለፅግ ተግቶ መስራት ነው ሲሉም ይደመድማሉ፡፡

       ተጠያቂው ማን ነው?

ከ100 በላይ የሚሆኑ ሰልጣኞች ራሳቸውን በገለፁበት መድረክ ብዙዎችን አንድ የሚያደርጋቸው ትውልዱ ላጣው ነገር ተጠያቂ ያደረጉት መንግስትን መሆኑ ነው፡፡  ከተሳታፊዎቹ ውስጥ አንዱ ብቻ ትውልዱ ያጣው ነገር የለም ብሏል፡፡ 85 እና ከዚያ በላይ የሚሆኑ ተሳታፊዎች ግን ትውልዱ ላጣው ነገር መንግስትን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡ የቀሩት እጅግ በጣም ጥቂት ተሳታፊዎች ደግሞ ተጠያቂው እራሱ ትውልዱ ነው ይላሉ፡፡ መንግስትን ተጠያቂ ያደረጉት ተሳታፊዎች ለምን መንግሥት ተጠያቂ እንዳደረጕት ያስረዳሉ፡፡ የተሳታፊዎች ሀሣብ ብዙ አይነት ቢሆንም ጠቅለል ባለ መልኩ የሚከተለውን አይነት ይዘት አለው፡፡
አንድ ዜጋ ሀገሩን ሊያገለግል የሚችለውና ያገር ፍቅርም የሚያድርበት እውቀት ሲኖረው ነው፡፡ ሀገሩንም ያለውን አቅም አውጥቶ እንዲጠቅም መማር ግድ ነው፡፡ መንግስት ግን ዜጐቹን እነርሱ የፈለጉትን ሳይሆን እርሱ የመረጠውን የትምህርት መስክ እንዲማሩ ማስገደዱ የወጣቱ እውቀት ውስንና ለውጤት የማያበቃ ከመሆኑም ባሻገር መንግስት ዜጎቹ እንዲያዉቁ የሚፈልግ አይመስለንም ያሉም አልጠፉም፡፡  በሚወዱትና በሚችሉት የትምህርት ዘርፍ ቢማሩ ብዙ ብቃት ያላቸውን ወጣቶች ማግኘት እንደሚቻልና ሀገርን መቀየርም እንደሚቻል ተሳታፊዎች ገልፀዋል፡፡ በሚፈልጉት የትምህርት ዘርፍ ካለመመደባቸዉ የተነሳ ብዙ ተማሪዎች የመማር ፍላጎታቸዉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ እንደሆነም አስረግጠዉ ተናግረዋል::ከዚህ ጋር ተያይዞም ሌላው መነሳት የሚገባው ነገር ተማሪዎች በሚፈልጉት የትምህርት ዘርፍ ቢመደቡም እንኳ የትምህርት ጥራት ጉዳይ ዜሮ እንደገባ ይገልፃሉ፡፡ ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩትም አዲስ አበባ ዮኒቨርሲቲን ሲተቹ የነበሩ ወጣቶች አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መማርን እንደ ውድቀት መግለፃቸው ለዚህ ማሳያ ነው፡፡ ሀሳባቸውን ሲያጠቃልሉም አሁን ያሉት ዩኒቨርሲቲዎች ቁጥራቸው ቢበዛም ገመናቸዉ ግን እውቀትን ለማስጨበጥ አቅም እንደሌላቸውና ንብ የሌለው ቀፎ እንደሆኑ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
ሌላው ትውዱ ላጣው ነገር መንግሥት ተጠያቂ ያደረጉት ሀሳቦች ሲነሱ ደግሞ በመንግስት መሥሪያ ቤቶች ያለው የስልጣን አደረጃጀት ተገቢ ያለመሆን ነው፡፡ ብዙ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች አመራሮቻቸው ለቦታው የማይመጥኑና ሥራውን በደንብ የማያውቁ እንደሆኑ ያብራራሉ፡፡ ስህተትን አምኖ ከመቀበል ይልቅ በውሸት ሪፖርት የተጠመዱ በመሆናቸው ለሀገሪቱ ለውጥ ያመጣሉ ማለት ታላቅ ሞኝነት ነው ብለው ይናገራሉ፡፡ እነርሱ /አመራሮች/ ይላሉ ተሳታፊዎች ዋናዉ አላማቸው እራሳቸውን ባቋራጭ ሀብታም ማድረግ እንጂ አዲስ ሀሳቦችን ለማስተናገድ ጆሮ የላቸውም ፡፡ ሙስናን የሚያጋልጥ ሰራተኛ በግምገማ ታፔላ እየተባረረ እያየን የእውነትን አስፈላጊነት ብናምንም እውነት በማይወደድበት መ/ቤቶች እውነትን መናገር ለመባረር ዝግጁ ከሆንን ብቻ ነው ሲሉም ይገልፃሉ፡፡ ውሎ አበል ያለው ስልጠና(ስብሰባ) ከመጣ በተለይም ውጭ ሀገር ከሆነ ከስልጠናው ጋር የማይገናኝ እውቀት ያለው አመራር ራሱን ወክሎ ይሄዳል፡፡ ውሎ አበል ከሌለው ግን ተራ ሰራተኞችን ነው የሚልከለው ብለው ያማርራሉ፡፡ ይህን ግራ የገባው አሠራር የሚመለከቱ ሠራተኞች ተሰላችተው ለሀገራቸው ያላቸው ፍቅር እየቀነሰ ሄዶ አሁን ኢትዮጵያዊ መሆንን ፈፅሞ እስከመጥላት እንደደረሱም አስታዉቀዋል፡፡
የመንግሥት ማዲያዎችም ከተጠያቂነት አላመለጡም፡፡ መንግስት ለግል ሚዲያዎች ትኩረት አለመስጠቱ የሕዝብ ሀሳቦች እንዳይንሸራሸሩ አድርጓል፡፡ ሁሌም በመንግስት ሚዲያዎች የሚራገበው ኘሮፓጋንዳ እንጂ ሀገርን የሚለውጡ አለመሆናቸዉን ይጠቅሳሉ፡፡ አንድ ተሳታፊ ይህንን ሲያስረዳ “ኢ.ቴ.ቪን እስኪ የሚያይ” ብሎ ጥያቄ ካነሳ በኃላ የራሱን ሀሳብ አስከተለ፡፡ ኢ.ቴ.ቪን እንደማያይ ከገለፀ  በኃላ ምክንያቱን ሲያስረዳም መገናኛ ብዙሀን የሚያስፈልጉት የሕዝብ አንደበት ለመሆን ቢሆንም ኢ.ቴ.ቪ የሚያቀርባቸው ሁሌም የመንግሥትን ፅድቅ የሚያበስሩና ቀድሜ የምገምታቸው በመሆናቸው ምን እንደሚተላለፍ እያወቅሁ ደግሜ ያንኑ መስማት ፋይዳ ቢስ ነው ብሏል፡፡ ሌሎች መገናኛ ብዙሀንም ቢሆኑ ብዙ ጊዜያቸውን በምዕራባውያን አርቲስቶችና ስፖርቶች የሚያጠፉ በመሆናቸው እኛም ሀገራችንን ረስተን ልባችን ወደ ምዕራብ እንዲያስብ እያደረግን ነው ይላል፡፡ አላማቸውም ህዝብ እንዳያውቅና ለማዘናጋት ይመስላል ብሎ ደምድሟል፡፡
አርአያ የሚሆን አመራር መጥፋቱም ሌላው የመንግስት ተጠያቂነት ነበር፡፡ ተሳታፊዎች አርአያ የሚያደርጉትን ሲናገሩ አብዛኞቹ ቤተሰቦቻቸውን፣የውጭ ሀገር መሪዎችን፣የቀድሞ ኢትዮጵያዊያን መሪዎችንና አርበኞችን እንዲሁም የውጭ ምሁራንን እንጂ አሁን ካሉት አመራር አርአያ የሚሆን መጥፋቱ ትውልዱ ላጣው ነገር እነደ አንድ ምክንያት ሆኗል፡፡
        መንግሥት ከማን ጋር ነው?
መንግሥት ብዙ እየሰራሁ ነው፣ዲሞክራሲን አስፍኛለሁ እያለ ሌት ከቀን ፉገራውን ቢዘራብንም ከተሳታፊዎች እንደሰማሁት ግን የመንግሥት አሰራር ፍፁም የመንግሥትን ሚና የማይመጥን መሆኑን ተገንዝቤአለሁ፡፡ ከመቶ ያህል ተሳታፊዎች ከ85 በላይ የሚሆኑት መንግሥትን ትውልዱ ላጣው ነገር ተጠያቂ ማድረጋቸው የመንግሥትን አላማ መሳት ያመለክታል፡፡ ታዲያ መንግሥት ከማን ጋር ነው? የእኔ የአመራር ፍልስፍና ተቀባይነት አለው ቢለንም የተገነዘብኩት ግን ፍልስፍናው ለሥራ እንቅፋት እንደሆነ ነው፡፡ እርግጥ ኢህአዴግ ራሱ አዲስ አበባ ላይ ብዙ አባላትና ደጋፊ እንደሌለው ያምናል፡፡ ግን ይህን ያህል ተቀባይነት እንዳጣ የተረዳሁት በዚሁ ውይይት ነበር፡፡ ምንም እንኳ ተሳታፊዎች መቶ ያህል ቢሆኑም ተሳታፊዎቹ ያላቸዉ የግል የትምህርት ደረጃቸውና የኑሮ ልምድ ኢህአዴግን የተማረ አይደግፈዉም የሚለዉ ሀሜት እዉነት እንደሆነ ያሳብቃል:: ስለሆነም  ኢህአዴግ በሌላው የተማረ ህብረተሰብ ዘንድም ተቀባይነቱን ጥያቄ ውስጥ ያስገባል፡፡ ሥለሆነም ኢህአዴግ ብቻውን እንደቀረ ተገንዝቤአለሁ፡፡ 
                                                      መፍትሄውስ?
መፍትሄው ያለው በራሱ በትውልዱ እጅ እንደሆነ ብዙዎች ተሳታፊዎች የገለጹ ሲሆን እኔም በዚህ እስማማበታለሁ፡፡ በዴሞክራሲ ማበብ እና ለኢኮኖሚ እድገት ድፍረትና ያገባኛል የሚል መንፈስ ማስረፅ ተገቢ ነው፡፡ መንግሥትን የማስተካከል ኃላፊነትም በህዝብ እጅ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ በወኔና በድፍረት ለመብታችን መቆምና የሾምነውን መንግስት የመቆጣጠር መብት ስላለን ሁሉም ኢትዮጵያዊ በውስጡ ሊያሰርፀው የሚገባ ተግባር እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ በመጨረሻም እናንተስ ከላይ በርዕሱ ለተነሱት ጥያቄዎች መልሳችሁ ምንድነዉ? 

Saturday, March 9, 2013

የስኬት ቁልፎች(The key to success)

ስኬት አንድ የታቀደ እቅድ(ግብ)በትክክል መፈፀም ማለት ነው፡፡ ከዚህ ዐረፍተ ነገረ መረዳት የምችለው ነገር ቢኖር ከስኬት በፊት ምንጊዜም የታቀደ ግብ ሊኖር እንደሚገባ  ነው፡፡ አንድ እቅድ ያላቀደ ሰው የፈለገው ቢሊዮነር አልያም ደግሞ የስልጣን ባለቤት ቢሆን እርሱ ስኬታማ ሊባል አይችልም:: በተመሳሳይ አንድ ተማሪ ኢንጅነር የመሆን ፍላጎትና አላማ እያለዉ ሳይፈልገዉና በትምህርት ሚንስቴር አስገዳጅነት ህክምና ገብቶ የተዋጣለት ዶክተር ቢሆን እርሱም ስኬታማ አይደለም::ምክንያቱም ስኬቱ ሊለካ የሚችለው ያቀደውን ግብ ከማሳካትና  እና አለማሳካት ጋር ነው፡፡ አንድ ለረጅም አመታት ለመግዛት ያቀደ ፓርቲ በጉልበትም ይሁን በዲሞክራሲያዊ መንገድ ያን ያቀደውን ያህል አመት ከገዛ ብቻ ነው ስኬታማ ሊባል የሚችው፡፡ ምናልባት ይህን እቅዱን ለማስካት የሚወስዳቸው እርምጃዎች ለህዝቡ ጎጂ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም ለህዝቡ የተሻለ ፓርቲ ቢመጣና ስልጣኑን ካቀደው አመት በፊት  ቢለቅ ለህዝቡ ጠቃሚ ሲሆን ስልጣን የለቀቀው ፓርቲ ግን ስኬታማ አይደለም፡፡ ይህ የፓርቲዎች ግብና የህዝብ ፍላጎት አለመጣጣም ነዉ ብዙዉን ጊዜ መሪዎች (በተለይም የአፍሪካ ) ምርጫ በመጣ ቁጥር የሚሸበሩት ስለሆነም አንድ ሰው/ድርጅት ግብ ሲያስቀምጥ ሌላውን የማይጎዳ መሆን ይገባዋል፡፡ ስኬት ግብ ለሚያቀምጡ ብቻ የተሠጠች ነች ማለት ነው፡፡ ለዚህም ነው “ If you fail to plan, you are planning to fail’ የሚሉት ምሁራን፡፡ከስኬት ቁልፎች መካከል አንዱ ግብ ማስቀመጥ(Goal setting) ሲሆን ሌሎች ደግሞ የዉስጥ መነሳሳት(Motivation) እና ጽናት (persistence) ናቸዉ::

       1.  ግብ ማስቀመጥ ( Goal setting)

ማንኛውም ስኬታማ መሆን የሚፈልግ ሰው እቅድ ማቀድ እንዳለበት ከተስማማን እቅዱስ ምን ምን ማሟላት አለባቸው? የሚለውን ጥያቄ ማንሳቱ ጠቃሚ ነዉ፡፡  ማንኛውም ዓይነት እቅድ “SMART ” መሆን አለበት:: ትርጓሜውም እንደሚከተለው ይተነተናል፡፡
S- Specific ( ግልጽና የተወሠነ)
M-Measurable (የሚለካ)
A- Achievable (ሊሳካ የሚችል)
R- Realistic (እውን ሊሆነ የሚችል)
T- Time framed ( በጊዜ የተወሰነ)

i)      specific ( ግልጽና የተወሠነ)

እቅድ (ግብ) በግልፅ የሚታወቅ መሆን ይገባዋል፡፡ ግልጽነት የሚጎድለዉ እቅድ እንዴት እንደምናሳካዉ ለማወቅ ከባድ ነዉ::ብዙ ሰዎች ግባቸውን ሲጠየቁ የተሻለየምትለዋን ቃል በማስቀደም ሌሎችን ፍላጎታቸውን ያስከትላሉ፡፡ የተሻለ ትምህርት፣ የተሻለ ቤት፣ የተሻለ ገቢ ፣የተሻለ የስልጣን ቦታ ወዘተ ይላሉ፡፡ ይህ አይነቱ ግብ ግልጽነትና ዉሱንነት ይጎድለዋል፡፡ ለስኬታማነትም ሊያበቃን አይችልም፡፡ እንደነዚህ አይነት ሰዎች ብዙ ጊዜያቸው የሚያጠፉት ከአንዱ አንዱ በመንከራተትና በመወዛገብ ነው፡ የተረጋጋ ህይወት ለእነርሱ ተረት ነው፡፡ የተሻለ ገቢ ለማግኜት የሚያቅድ ሰውና የ3000 ብር ደመወዘኛ የ3200 ብር ደመወዝ ያለው የስራ ማስታወቂያ ከወጣ ያለ ጥርጥር ስራውን ይቀይራል፡፡ ምክንያቱም እቅዱ የተሻለ ማግኜት ነውና፡፡ ለዚህም ነው እንዳንድ ሰዎች ከእድሜያቸው በላይ መስሪያ ቤት ሲቀያይሩ የሚኖሩት፡፡ በተመሳሳይ የተሻለ ትምህርት የሚፈልግና ዲግሪ ያለዉ ሰው በአጋጣሚ መንገድ ጠፍቶበት በዩኒቨርሲቲ በር ሲያለፍ የድህረ-ምረቃ ትምህርት ማስታወቂያ ቢያነብ ትምህርቱ ይጥቀመውም አይጥቀመውም ዘሎ ገብቶ ይመዘገባል፡፡ ተምሮ ሲወጣ ግን በህይወቱ ምንም ዋጋ ላይጨምር ይችላል፡፡ በአጠቃላይ ግብ በግልጽ ተወስኖ የተቀመጠ መሆን ይገባዋል፡፡ የተሻለ ገቢ በማለት ፈንታ በወር ማግኜት የሚፈልገውን የገንዘብ መጠን ቢያቀምጥ ይመረጣል፡፡ የተሻለ ትምህርት በማለት ፈንታም ዲግሪ፣ ማስተርስወይም ፒ.ኤች. ዲ እና የመሣሰሉትን ቢያቀምጥ ይመረጣል፡፡

ii). Measurable (የሚለካ)

ሌላው ግብ ስናስቅምጥ ማስተዋል የሚገባን ነገር ግባችን የሚለካ መሆን አለበት፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰዎችን የሚረዳ ድርጂት ለማቋቋም ያቀደ ሰው ምን ያህል ሰዎችን እንደሚረዳ በግልፅ ማስቀመጥ አለበት፡፡ ቤት ለመሰራት ያቀደም ሰው ቢሆን የቤቱን ስፋት አይነት እና የመሳሰሉትን በግልፅ  ማስቀመጥ አለበት፡፡ አለበለዚያ አንድ ሰው ብቻ የምታሰገባ ቤት ቢሰራም ቤት ቤት ነውና እቅዱን እዳሳሣካ ሊቆጥረው ይችላል፡፡ በመሆኑም ማንኛውም ግብ የሚያስቀምጥ ሰው ግቡ የሚለካ መሆን አለበት፡፡

iii)      Achievable (ሊሳካ የሚችል)

አሁንም ግብ ስናስቀምጥ ግባችን ሊሳካ የሚል መሆኑን ማረጋገጥ አለብን፡፡ ይህን በምሳሌ ለማስረዳትም አንድ የ7ኛ ክፍል ተማሪ ዛሬ ላይ ሆኖ የዛሬ 10 ዓመት ፒ.ኤች.ዲ ዲግሪዉን እንደሚይዝ ቢያቅድ እቅዱ ሊሳካ የሚችል አይደለም፡፡ ምክንያቱም ስርዓተ-ትምህርቱ ከ7ኛ ክፍል ወደ ፒ.ኤች.ዲ. ዲግሪ በ10 ዓመት ያጠናቅቅ ዘንድ አይፈቅድለትም፡፡ በኢትዮጵያ ስርዓተ ትምህርት መሠረት ከ7ኛ ክፍል ፒ.ኤች.ዲ. ዲግሪ  ለመያዝ ቢያንስ 14 ዓመታትን ይፈጃል፡፡ ስለሆነም ይህን እቅድ ያቀደ ሠው እቅዱን ሊያሳካ አይችልም፡፡ ስለዚህም ሁጊዜ ግብ ስናስቀምጥ ሊሳካ የሚችል መሆኑንና አለመሆኑን ማሠብ ይኖርብናል፡፡

iv)      Realistic  (እውን ሊሆን የሚችል)

አራተኛው ግብ ሊያካትተው የሚባው መስፈርት ደግሞ እውን ሊሆን የሚችል መሆኑን ነው፡፡ ይህ ቀጥታ ከተፈጥሮ ጋር የሚያያዝና ልንቀይራቸው የማንችላቸውን ነገሮች ማቀድ እንደሌለብን የሚያስገነዝብ ነው፡፡ “change the changeable, accept the unchangeable” 
እንዲሉ ምሁራን በተፈጥሮ እውን ሊሆን የማይችልን ነገር ማቀድ ድካሙ ነው ትርፉ፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው “የዛሬ ዓመት መልዓክ ለመሆን ቢያቅድ እቅዱ እቅድ መሆኑ ቀርቶ ቅዠት ነው የሚሆነው፡፡ ስለሆነም ግባችን በገሃዱ አለም እውን ሊሆን የሚች መሆን አለበት፡ 

v)     Time framed ( በጊዜ የተወሰነ)

 የመጨረሻውና ግብ ስናስቀምጥ ማካተት ያለብን ነገር ግባችን በጊዜ-የተወሰነ መሆኑን ማረጋገጥ ነው፡፡ ይህ ችግር ከሌሎች ማሟላት ከሚገቡን ነገሮች የበለጠ ጎልቶ የሚታይ ነው፡፡ “መኪና ሳልገዛማ አልሞትም” ሲል የምንሠማው ሰው መኪና መቼ እንደሚገዛ ግን አያውቀውም፡፡ የዛሬ 20 አመትም ይህንን ሲደግመው እናሠማለን፡፡ ግብ ስናስቀምጥ ምን ጊዜም በጊዜ የተወሰነ መሆን ይኖርበታል፡፡ አለበለዚያ ነገ እሠረዋለሁ እያልን እድሜያችንን መፍጀታችን ነዉ፡፡
በአጠቃላይ ለስኬት አንዱ ቁልፍ ግብ ማስቀመጥ ሲሆን ግብ ስናስቀምጥም እነዚህን 5 ነገሮች ማካተት አለበት፡፡ ግባችን እነዚህን ነገሮች ሲያሟላ እያንዳንዱ እንቅስቃሴያችን ግባችንን ከማሳካት ጋር ይሆናል፡፡
እነዚህ ማንኛውም ግብ ሊያሟላቸው የሚገቡ ነገሮች ቢሆኑም የበለጠ ስኬታማ ለመሆን ተጨማሪ በግብ ውስጥ መካተት እንዳለባቸውም የተለያዩ ምሁራን ይናገራሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የተወሠኑትን ለመጥቀስ ያህል ግብ በምናስቀምጥት ጊዜ ግባችን ሰፊ መሆን አለበት፡፡ ግባችን በጣም ትንሽ  ከሆነች በቁርጠኝነት እንድንሠራ እያደረገንም፡፡ የ200 ብር የገቢ ጭማሪ ብናቅድ ይህን እንዳሣካን ባለንበት ቀጥ ብለን ነው የምንቀረው፡፡ ስለዚህ ግባችን ሠፊ መሆን አለበት:: ሌላው ግባችን ማካተት ያለበት ነገር ደግሞ ዉጣ ውረድ የሚጠይቅ መሆኑን ማረጋገጥ አለብን፡፡ ስኬት የዉጣ ውረድ ውጤት ነው፡፡ ነገሮች አልጋ በአልጋ ከሆኑልን ብዙም ውጤታማ አንሆንም፡፡ የተወሳሰቡ ሰራዎችን የሚከተል ግብም ተመራጭ ነው፡፡ ሁሌ ተመሳሳይ የሆነ ነገር ስንሠራ ብዙዎቻችን እንሰለቻለን፡፡ በመሆኑም የበለጠ ስኬታማ ለመሆን ግባችን ውስብስብ ስራዎች የሚፈልግ መሆን አለበት፡፡ 

     ሰዎች ለምን ግብ አያስቀምጡም? 

ስኬታማ መሆንን የማይፈልግ ሰው ይኖራል ብሎ ማሠቡ ተገቢ ባይሆንም ግብ የማናስቀምጥ ግን ብዙዎቻችን ነን፡፡ ከስኬት ቁልፎች አንዱ ግብ ማስቀመጥ እደሆነም ከላይ ለማየት ሞክረናል፡፡ ነገር ግን ግብ ሳያስቀምጡ ስኬት ላም አለኝ በሰማይነው፡፡ ታዲያ ሰዎች ለምን ግብ አያስቀምጡም? ብለን መጠየቅ ያሥፈልገናል፡፡
ግብ ላለማስቀመጥ ዋናው ምክንያት የምንፈልገውን አለማወቅ ነው:: ማንኛውም ሰው የሚፈልገውን ማወቅ ቀላል መስሎ ሊታየው ይችላል፡፡ ነገር ግን የምንፈልገውን በትክክል ማወቅ እጅግ አስቸጋሪ ነገር ነዉ::ምክንያቱም ፍላጎታችን በየጊዜዉ የሚቀያየር በመሆኑ ነዉ::ለዚህም  ነው ያየነው ሁሉ የሚያምረን፡፡ የሚያዝናና ኳስ ስናይ እግር ኳስ ተጨዋች መሆን ያምረናል፣ የኦሊምፒክ ሰሞን ደግሞ ሯጭ መሆን ያምረናል፡፡ ፊልም ስናይ አርቲስት መሆን እንፈልጋለን፣ አንድ የፈጠራ ስራ ስናይ ጥሩ ኢንጂነር መሆን ያምረናል፣ የሲ አይ.ኤ ንና ሞሳድን ዝና ስንሰማ ሰላይ መሆን ይከጅለናል ::የተሳካ ቀዶ ጥገና ስንሰማ ደግሞ ዶክተር መሆን በእጅጉ እንመኛለን:: አሪፍ ህንፃ ስናይ ባለ ሐብት መሆን እንቋምጣለን፡፡ ኧረ ስንቱ…፡፡ ስለዚህ  የእኛ ትክክለኛ ፍላጎት የትኛው ነው? ፍላጎታችንን በትክክል ካወቅን ግብ ማስቀመጥ አይከብደንም፡፡ “ነገር በምሳሌ ጠጅ በብርሌ” እንዲሉ አንድ ወጣት የስኬታማነትን ቁልፍ ለማወቅ ፈልጎ ዝነኛውን የግሪኩ ፈላስፋ ሶቅራጥስን የስኬትን ቁልፍ እንዲነግረው ጠየቀዉ ይባላል፡፡ ሶቅራጥስም ወጣቱን ና እየሄድን እነግርሃለሁ ብሎ በባህር ውስጥ እየተራመዱ መሄድ ጀመሩ ፡፡ እየሄዱ እያለም ሶቅራጥስ ወጣቱን ምን እንደሚፈልግ ዳድም ይጠይቀዋል፡፡ ወጣቱም የስኬት ምስጢርን እንድትነግረኝ ፈልጌ ነው ይለዋል፡፡ ባሕሩ መሀል እንደደረሱ ሶቅራጥስ ወጣቱን አንገቱን ይዞ አሰጠመው፡፡ ወጣቱም አየር ለማግኘት ይፈራገጥ ጀመር፡፡ ሶቅራጥስ ግን ሊለቀው አልቻለም፡፡ ወጣቱም ኧረ እባክህ ልቀቀኝ ልትገለኝ ነው እያለ ቢጮህም ሶቅራጥስ አለቀቀውም፡፡ ከጥቂት ደቂቃ በኋላ ሶቅራጥስ ወጣቱን ከውሃው አወጣውና ለምን ይፈራገጥ እንደነበርና እንዲለቀው የጠቀበትን ምክንያት ይጠይቀዋል፡፡ ወጣቱም አየር ፈልጌ ነዉ ይለዋል፡፡ሶቅራጥስም ወጣቱን “አየህ አየር እንደሚያስፈልግሀ ስታውቅ እንደዚህ ከተፈረገጥክ ስኬታማ መሆን ከፈለግህም መጀመሪያ ምን እንደምትፈልግ እወቅ” ብሎ መለሰለት ይባላል፡፡ ስለዚህም ወደ እንቅስቃሴና ትጋት የምንገባው ውስጣችን እንድናገኘዉ የሚፈልገዉን ነገር ማወቅ ስንችል ነው፡፡ ማንኛውም ስኬታማ መሆን የሚፈልግ ሰው በመጀመሪያ ፍላጐቱን ማወቅ ግድ ይለዋል፡፡ ነገሩን ስናጠቃልለው ሰዎች ግብ የማያስቀምጡበት ዋነኛው ምክንያት ፍላጐታቸውን ማወቅ አለመቻላቸው ነው፡፡ ግብ ከማስከመጣችን በፊት ፍላጐታችንን ጠንቅቀን ማወቅ ታላቅ የቤትሥራ ይሆናል፡፡

  2. የውስጥ መነሳሳት (Motivation) 

ግብ ስላስቀመጥን ብቻ ስኬታማ እንሆናለን ማለት አይደለም፡፡ ግባችንን ለማሳካት ያላሰለሰ ጥረት ያስፈልገናል፡፡ በመሆኑም ሁለተኛው የስኬት ቁልፍ ውስጣዊ መነሳሳትን መፍጠር ነው፡፡ ይህን ውስጣዊ መነሳሳታችንን ለማምጣት ደግሞ ያቀድነውን እቅድ በተለያዩና ሊታዩን በሚችሉ ቦታዎች ማስቀመጥ  ይመከራል፡፡ ያስቀመጥነው ግብ ሁልጊዜ ስናየው የበለጠ ለመስራት እንነሳሳለን፡፡ ሌላው ውስጣችንን ለማነሳሳት ልንጠቀምበት የምንችለው ነገር ግባችንን ካሳካን በኋላ ልናገኘው የምንችለውን ስሜት በማሰብ ነው፡፡ ግቤን ሳሳከ ምን አያለሁ፣ምን እሰማለሁ፣ ምንአይነት ስሜት ይሰማኛል የሚሉትን ጥያቄዎች ሁል ጊዜ በማንሳት ውስጣዊ መነሳሳትን ልናመጣ እንችላለን፡፡ 

3     3 .  ፅናት (persistence)

   ስኬት ጽናት ለሌላቸዉ ጀርበዋን የምትሰጥ ወይዘሮ ናት፡ከእያንዳንዱ ስኬታማ ሰዉ በስተጀርባ ጽናት ይኖራል፡፡ነገሮች ሁሉ አልጋ በአልጋ ሆነዉለት ስኬታማ የሆነ ማግኜት ይከብዳል፡፡  በምሳሌ ለማስረዳት ያህልም ሁለት ዋሽንት የሚነፉ ሰዎች ነበሩ ይባላል፡፡አንደኛዉ ሲነፋ ሁሌም ዝናብ ይዘንባል ፡፡ሌላኛዉ ሲነፋ ግን አይዘንብም፡፡ዋሽንት ሲነፋ ዝናብ በሚዘንብለት ሰዉ የሚያዩት ሁሉ ይገረሙበታል፡፡ ሁለቱም ግን ተመልካች አላቸዉ፡፡ከእለታት በአንድ ቀን ዋሽንት ሲነፋ ዝናብ የማይዘንብለትን የሚመለከቱት ሰዎች ሲነፋ የሚዘንብለትን የሚመለከቱትን ሰዎች ዋሽንት ሊያሰሙዋቸዉ ጋበዙዋቸዉ፡፡ተጋባዦችም ዋሽንቱን ከሰሙ በሁዋላ ለጋበዙዋቸዉ ሰዎች እነርሱም በተራቸዉ ዋሽንት ሲነፋ ዝናብ የሚዘንብለትን ሰዉ ያዩት ዘንድ ጋበዙዋቸዉ:: ተጋባዦች ሲያዩ ሰዉዬዉ ሲነፋ ከቆየ በሁዋላ ዝናብ ይዘንብ ጀመር::  በጣም ተገረሙ ::ዋሽንት የሚነፋዉንም ሰዉየ እርሱ ሲነፋ ለምን ዝናብ እንደሚዘንብ ይነግራቸዉ ዘንድ ጠየቁት::ሰዉዬዉም "አይ እኔ ስነፋ አይደለም ዝናብ የሚዘንበዉ ነገር ግን ዝናብ እስከሚዘንብ ነዉ የምነፋዉ"ብሎ መለሰላቸዉ ይባላል::አዎ እኛም ያቀድነዉ እስከሚዘንብልን ድረስ መጽናት ያስፈልገናል:: ይህ ካልሆነ ግን ስኬትን ማምጣት ከባድ ነዉ::በመጨረሻም 
      "CHANGE YOUR WAY BUT NOT YOUR GOAL" ብዬ ላብቃ
              መልካም የስኬት ጊዜ!!!